ማንቸስተር ዩናይትድ የቼልሲውን አማካይ አንድሬይ ሳንቶስን ለማስፈረም ፍላጎት አሳየ

ማንቸስተር ዩናይትድ የቼልሲውን አማካይ አንድሬይ ሳንቶስን ለማስፈረም ፍላጎት አሳየ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 28/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የአማካይ ክፍሉን ለማጠናከር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬይ ሳንቶስን ከቼልሲ ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል።

በካሴሚሮ ክለቡን መልቀቅ እንዲሁም በዓለም ዋንጫው ላይ ማኑኤል ኡጋርቴ ከባድ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት የመሐል ክፍሉ የሳሳበት ዩናይትድ በዚህ ክረምት በትንሹ እስከ 3 የሚጠጋ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ያስፈርማል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ የተመለሱት ቀያይ ሰይጣኖቹ ኤደርሰንን ከአታላንታ በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

ተጨማሪ አማካዮችን ለማስፈረም በገበያው ላይ በመንቀሳቀስ ኤሊዮት አንደርሰንን እና ማቲያስ ፈርናንዴዝን ለማስፈረም ተንቀሳቅሶ በሌሎች ክለቦች የተቀደመው ማንቸስተር ዩናይትድ ፉቱን ወደ ሌላኛው ብራዚላዊ አማካይ አንድሬይ ሳንቶስ ላይ ማዞሩን ዘጋርዲያን አስነብቧል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከተጫዋቹ ዝውውር 50 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲከፈለው ይፈልጋል።

ተጫዋቹ በሰማያዊዮቹ ቤት በቋሚነት የመሰለፉ ዕድል ጠባብ መሆኑን ተከትሎ ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልግ ተነግሯል።

የ22 ዓመቱ አንድሬይ ሳንቶስ ቼልሲን በ2023 ከብራዚሉ ክለብ ቫስኮ ደጋማ በ18 ሚሊዮን ፓውንድ መቀላቀሉ የሚታወስ ነው።

ለንደኑ ክለብ ከፈረመ በኋላ ለኖቲንግሃም ፎረስት እና ስታራስቡርግ በውሰት ተሰጥቶ ተጫውቷል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ