በስነ ምግባር የታነጸ፣ ሀገር ወዳድ እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ከመሰረቱ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

በስነ ምግባር የታነጸ፣ ሀገር ወዳድ እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ከመሰረቱ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ: ሰኔ 28/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በስነ ምግባር የታነጸ፣ ሀገር ወዳድ እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ከመሰረቱ መስራት እንደሚገባ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድአሚን በደዊ ገለጹ።

በቀቤና ልዩ ወረዳ በሩሙጋ ቀበሌ ከ21ሚሊየን 700ሺ ብር በላይ የተገነባው የቅድመ መደበኛ የነገው ትውልድ ትምህርት ቤት አካዳሚ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኖአል።

በአካዳሚው ደረጃቸውን የጠበቁና ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢ የሚፈጥሩ የመማሪያ ክፍሎች በመሆናቸው ህጻናትን በእወቅትና ክህሎት ኰትኮቶ ለማብቃት ጉልህ ድረሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በምርቃት ስነስረአቱ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድአሚን በደዊ በስነ ምግባር የታነጸ፣ ሀገር ወዳድና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር እንዲሁም ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ከመሰረቱ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሁሉም ዘርፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት እና በሃገሪቱ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የሚያስቀጥሉ ዜጎችን ለመፍጠር የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ አጽዕኖት ሰጥቶ መስራት እንደሚያሻም ገልፀዋል።

በዚህም አካዳሚው በልዩ ወረዳው በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ለሚደረገው ጥረት እገዛው ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።

አካዳሚው የተለያዩ አስፈላጊ እና መሰረታዊ የትመህርት ግበአቶችን ያሟላ በመሆኑ የልዩ ወረዳው ነዋሪዎችና ሌሎችም የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆቹን በማስተማር እድሉን ሊጠቀምበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው ህብረተሰቡ ለረጅም አመታት ሲጠይቃቸው ከነበሩ የልማት ጥያቄዎች መካከል አንዱ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ እንደነበር አስታውሰው ይህም ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝን በማድረግ የነገው ትውልድ አካዳሚ ባለቤት ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ነገር መሰረት የሚጥል በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን በተገቢው መንገድ በማስተማር ሃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።

የነገው ትውልድ አካዳሚ ባለቤት አቶ አንዋር ሙደሲር እንደገለፁት ምህርት ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በትምህርት ልማት ዘርፎች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል።

በዚህ ዘርፍ የተሰማራነው በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ለነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ለሚደረገው ርብርብ የራሳችንን አሻራ ለማኖር ነውም ብለዋል አቶ አንዋር ሙደሲር።

በምርቃት ስነስረአቱ ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቤቱ መገንባት የቅደመ መደበኛ ትመህርት ቤት አጥቶ ሲቸገር ለነበረው የአካባቢው ማህበረሰብ እፎይታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

አካዳሚው በቅርበት በመገንባቱ እና የተለያዩ እንግልቶችን የሚያስቀር በመሆኑ መደሰታቸውንም ተናግረዋል።

በመጨረሻም ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ቃል በአካዳሚው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ተከናውኗል

ዘጋቢ: አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን