ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እግር ኳስ መጫወትን ለመተው አስቦ እንደነበር ገለጸ

ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እግር ኳስ መጫወትን ለመተው አስቦ እንደነበር ገለጸ

የማንችስተር ዩናይትድ እና የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ካሳለፋቸው በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት አንዱን ይፋ አድርጓል።

ተጫዋቹ ባለፈው አመት የደረሰበት የጉልበት (ACL) ጉዳት፣ በስነ-ልቦናው ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠሩ እግር ኳስ መጫወትን እስከማቆም ደርሶ እንደነበር ተናግሯል።

ሊሳንድሮ ከዚህ ቀደም የነበረበት ጉዳት ሳይበቃው፣ የ ACL ጉዳቱ ሲጨመርበት ተስፋ መቁረጡን ሲያስታውስ”ባለፈው ዓመት የደረሰብኝ የ ACL ጉዳት በጣም ከባድ ነበር።

ቀደም ሲልም የነበሩኝ የእግር ጉዳቶች ነበሩ፣ ነገር ግን ይህኛው እጅግ የከፋው ነው። ከአሁን በኋላ መከራን መቀበል አልፈልግም ነበር፤ በመሆኑም ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ለመገለል በቁም ነገር አስቤ ነበር” ሲል ገልጿል።

ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ለድጋሚ መነሳሳቱ ሌላው ትልቅ ምክንያት በብሔራዊ ቡድን የቡድን አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ መሆኑን ጠቅሷል።ሜሲ በ 39 ዓመቱ ሳይሰለች የሚያሳየው ጥረት ለማርቲኔዝ ትልቅ ትምህርት ሆኖታል።

“ጉዳት በደረሰብኝ ጊዜ ሁሌም የማስበው ሜሲን ነበር” የሚለው ማርቲኔዝ “እሱ ሁሉንም ነገር አሸንፏል፤ ምንም የሚያረጋግጠው ነገር የለም።

ሆኖም አሁንም ድረስ በዛ አይነት ስሜት እና ፍቅር ሲታገል እናየዋለን። እሱ በታሪክ የሁሉም ስፖርቶች ምርጥ ተጫዋች ነው። እሱ በዚህ ሁኔታ ከታገለ፣ እኛ እንዴት ትግላችንን እናቆማለን? የእሱን ፈለግ መከተል ግዴታችን ነው” በማለት ተናግሯል።

የሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ይህ ምስክርነት፣ የተጫዋቾች የስነ-ልቦና ጥንካሬ ከስፖርታዊ ብቃት ባሻገር በግል ህይወት ውስጥ በሚያገኙት መነሳሳት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ