ሀዋሳ፡ ሰኔ 26/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበጀት ዓመቱ በመንገድና በድልድይ ግንባታ ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት መከናወኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ምስጋናው ማቲዮስ ገለፁ።
የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ምስጋናው ማቲዮስ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በበጀት ዓመቱ አዳዲስ የጠጠር መንገዶች ግንባታ፣ የነባር መንገዶችን ጥገና እንዲሁም የድልድይ ግንባታ በማከናወን ረገድ የተሻለ ዉጤቶች መመዝገቡን አመላክተዋል።
በበጀት አመቱ ስራዎችን በቅልጥፍና ለማከናወን የነዳጅ አቅርቦት ችግር እክል ቢፈጥርም ፈተናዎችን በመሻገር እየተከናወኑ የነበሩ ፕሮጀክቶች እንዳይቆሙ የጋራ እርብርብ መደረጉንም ተናግረዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ተደርጓልም ብለዋል።
በዚህም በመንገድና በድልድይ ግንባታ ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ኢንጂነር ምስጋናው አስረድተዋል።
ጅምር ላይ ያሉ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ስራዎችን ለማጠናቀቅ የቁጥጥር ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
በ2018 በጀት አመት የታዩ ወስንነቶችን በመለየት እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት በቀጣይ የተሻለ ስራ እንደሚሰራም አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ የመሰረተ ልማትና የመንግስት ሃብት ቁጥጥር ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታመነ ገብሬ በበኩላቸው በመንግስት የሚመደቡ በጀቶች ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ለማድረግ የፋይናንስ አሰራር ግልፀኝነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የሚሰሩ መንገዶች እና ድልድዮች ጥራትና ዘላቂነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የክትትል ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅና የመንገድ ግንባታ እና ጥገና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወሰኔ ባሻ በ2018 በጀት አመት በክልሉ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አስታውቀዋል።
በተለያየ ምክንያት ግንባታቸው የዘገዩ 7 ድልድዮች ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን 1ሺህ 746 ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገኑንም አስረድተዋል። በመድረኩ የባለስልጣኑ እና 4ቱም ዲስትሪክቶች የ2018 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበው በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመንገድና በድልድይ ግንባታ ዘርፎች በተሰሩ የቅንጅት ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተለያየ ጊዜ ግንባታቸው የዘገዩ እንዲሁም የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ በቅንጅት መስራት እንደሚያሻም አውስተዋል።
ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ313 ሺህ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰራጭቷል – የክልሉ ግብርና ቢሮ
ሀገራዊ ምክክር፤ የመደማመጥ፣ የመግባባትና የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት ነው!
ከ23 ሚሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ተገለጸ