መሬት የኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ በጥንቃቄ ሊመራ እንደሚገባ ተገለፀ

መሬት የኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ በጥንቃቄ ሊመራ እንደሚገባ ተገለፀ

‎መሬት ከሁሉም ሀብቶች የላቀ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ በአግባቡና በጥንቃቄ ሊመራ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።

‎ይህ የተገለጸው ቢሮው በዲላ ከተማ ባካሄደው የ2018 በጀት ዓመት የመሬት አስተዳደር ሴክተር የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ነው።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ ቢሆንም የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን በማጠናከርና የተበታተኑ አሠራሮችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን
‎የቢሮው ምክትልና የመሬት አጠቃቀምና የጂኦ ስፓሻል ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ዮሴፍ ማሩ ገልፀዋል።

‎እንደ ሀገር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር መሬት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፣ በተለይም በገጠር መሬት የሕግ ማዕቀፎችን በመተግበርና የመሬት አስተዳደርን በማዘመን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

‎በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ጥላሁን፤ በዞኑ በሁሉም ገጠርና ከተማ አካባቢዎች የመሬት ልኬት በማከናወን አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

‎አቶ ፍቃዱ፥ ቢሮው በየጊዜው የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ለተሻለ ውጤት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

‎በመድረኩ የ12 ዞኖችና የ3 ሪጂኦ ፖሊሲ ከተሞች የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች እየቀረቡ ነው።

‎ዘጋቢ: ውብሸት ኃይለማሪያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን