በከተማው የእብድ ውሻ በሽታ መስፋፋትን ተከትሎ ባለቤት ላላቸው ውሾች ክትባት በመስጠት ባለቤት አልባዎቹን የማስወገድ ስራ ለመስራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ

በከተማው ስርዓቱን ባልተከተለና ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የውሾች ግድያ በፍጥነት እንዲቆም መደረጉም ተገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ስሞኑን አለአግባብ ከተፈፀመው ከውሻ ግድያ ጋር ተያይዞ የሚናፈሱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመለየት እንዲሁም የተከተቡ ውሾችን በማሰር እና በተገቢው በመያዝ ለሰው እና ለእንስሳት ጤና የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ተጠቁሟል።

ሰሞኑን በሆሳዕና ከተማ የተከሰተውን ጥንቃቄ የጎደለው የውሾች ግድያ አስመልክተው በሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ለፋሞ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ በአስሩም ቀበሌያት የሚገኙ ውሾችን መረጃ የማደራጀት ስራ ተሠርቷል።

በዚህም 7 ሺ 5 መቶ ባለቤት ያላቸውን እንዲሁም ሶስት ሺህ በላይ ባለቤት የሌላቸውን ውሾች በአጠቃላይ 10 ሺ 5 መቶ በላይ ውሾች በከተማው መኖራቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማው የእብድ ውሻ በሽታ ከመስፋፋቱ የተነሳ በሰው ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ በበጀት አመቱ በከተማው በአምስት ማዕከላት በሶስት ዙሮች ለ7 ሺህ 2 መቶ ባለቤት ላላቸው ውሾች የመከላከያ ክትባትና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መሰጠቱን የገለጹት አቶ ተመስገን፤ ቀሪዎቹን 3 መቶ ባለቤት ያላቸውን ውሾች ለማስከተብ የመድኃኒት እጥረት የተከሰተ በመሆኑ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ባለቤት አልባ የሆኑ ከ3 ሺህ በላይ የጎዳና ውሾችን ከህጎችና አዋጆች ጋር በማይቃረን መልኩ ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።

የባለድርሻ አካላት የጋራ ውይይት ያስፈለገበት ምክንያትም አዲስ የወጣው 1376/2017 አዋጅ ውሾችን በመርዝ መግደልን የሚከለክል በመሆኑ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በከተማው በውስን አካባቢዎች የውሾችን መብት በተጋፋና ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በመግደል የተፈጸመው ድርጊት አግባብነት የሌለው መሆኑንም አንስተዋል።

በእብድ ውሻ በሽታ ምክንያት የሰው ህይወት የጠፋባቸው አካባቢ ነዋሪዎችና እና ዕድሮች በተፈጠረው የሞት ድንጋጤ የተነሳ ህፃናትን ጭምር በማሳተፍ በውሾች ላይ የተደረገው ግድያ አግባብነት የሌለው እንደሆነ የገለጹት አቶ ተመስገን ይህ ድርጊት የበሽታውን ስርጭት ይበልጥ የሚያስፋፋ መሆኑን በመገምገም ድርጊቱ በፍጥነት እንዲቆም መደረጉንም አሳውቀዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ውሻ እንዲገደል እና ያላስገደለ የውሻ ባለቤት ሃምሳ ሺህ ብር ቅጣት ይጣልበታል ተብሎ በአንዳንድ ግለሰቦችና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር የነበረው መረጃም ፍጹም የተሳሳተ እንደሆነም ሃላፊው አብራርተዋል።

በሌላ ጎኑ ለውሾቹ ክትባት የሚውል መድኃኒት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር

በየደረጃው በመነጋገር በህጋዊ መንገድ የቀረበ ሆኖ ሳለ ውሾቹ የተከተቡበት መድኃኒት ጊዜ ያለፈበት እና የማይሰራ ነው ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ አሉባልታ መሆኑንም አቶ ተመስገን አክለዋል።

ይልቅ ለማህበረሰቡ ጤና ጠንቅ እየሆነ ያለው የክትባት መድሃኒቱ ሳይሆን የተከተቡ ውሾችን በቤት ውስጥ አስሮ ያለመንከባከብ እና በጎዳና መልቀቅ በመሆኑ የውሻ ባለቤቶች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአሁኑ ጊዜ የእብድ ውሻ በሽታ መስፋፋቱን ተከትሎ የጎዳና ውሾችን ለማስወገድ በተለመደው መንገድ በመርዝ መግደልን አዲሱ አዋጅ የሚከለከል በመሆኑ በአወጋገድ ስርዓቱ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ያሉት ኃላፊው ያለአግባብ ግድያዎች በፍጥነት እንዲቆሙ በመግባባት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል።

የውሻ ክትባትም ሆነ የውሻ ንክሻ ለገጠማቸው ሰዎች የሚሰጥ መድሃኒት እጥረትን በተመለከተ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎ መፍትሄ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ለውሻ ክትባት በሚወጣ ፕሮግራም መሰረት ባለመዘናጋት የራሱን ውሻ ማስከተብና አስሮ መጠበቅ እና የውሻ ንክሻ የገጠማቸውን ሰዎችን በፍጥነት ወደህክምና ተቋማት መውሰድ እንደሚገባም ኃላፊው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን