በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ አስተባባሪነት የ2018 ዓ.ም የመኸር ወቅት የተቀናጀ የግብርና ስራዎች ንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ አስተባባሪነት የ2018 ዓ.ም የመኸር ወቅት የተቀናጀ የግብርና ስራዎች ንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል

መድረኩ “የተቀናጀ ግብርና ትጋት ለላቀ ምርታማነት” በሚል መሪ ቃል የተካሂደ ሲሆን፣ በዞኑ የሚገኙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ግብርና የሁሉም ልማቶች መሰረት በመሆኑ የምርትና ምርታማነትን ዕድገት ለማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የግብርና ስራ የባለሙያዎች ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም በማለት፣ የታቀዱ ተግባራትን በአግባቡ ፈጽሞ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች ቅንጅትና ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አቶ ማቴዎስ አክለውም፣ አርሶ አደሩ በመሬት ዝግጅትና በግብዓት አቅርቦት ረገድ በቂ ዝግጅት በማድረግ ጥራትና መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ምርት ማምረት እንዳለበት ጠቅሰው፣ ይህም የገጠርና የከተማን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው አመላክተዋል።

በምርት ሂደት ላይ እንቅፋት እየሆኑ ያሉ የአሰራር ክፍተቶችን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን በአግባቡ የመጠቀም ልማዱ ሊቀየር እንደሚገባና ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ሰፊው አርሶ አደር የማስፋት ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በእርሻ ስራው ላይ ተጽዕኖ በሚፈጥሩ የመሬት አስተዳደር ክፍተቶችና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራዎች ላይ ጠንካራ የክትትልና የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

ለእርሻ ስራው ወሳኝ የሆነው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በትክክለኛው ጊዜና መጠን መድረሱን ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የኢኮኖሚ አቅምን በሚገነቡ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች ተከላ ላይ ልዩ ትኩረት ተደረጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስራው በዘፈቀደ ሳይሆን በተደራጀና ከአካባቢ ጥበቃና ከደን ልማት ስራዎች ጋር በተሳሰረ መልኩ ሊመራ እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል።

ለመድረኩ የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ታደሰ በበኩላቸው፤ በ2017/18 ምርት ዘመን የመኸር ወቅት ከ156 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ7.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንና ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር መለማቱን ገልጸዋል።

በ2018/19 ምርት ዘመን ደግሞ ከ179 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ8.7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንና ለዚህም የምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያና አግሮ ኬሚካል አቅርቦት በልዩ ሁኔታ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ይህ የንቅናቄ መድረክ የወቅቱን ስራ ለመምራት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ በመድረኩ የተነሱ አቅጣጫዎችንና ጠንካራ የንቅናቄ መንፈስን ወደታችኛው መዋቅር በማውረድ በተግባር ለመተርጎም ሙሉ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ : ታምራት አለሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን