የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቦንጋ ከተማ አስተዳደር ተጀመረ
አገልግሎቱ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ሲሆን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ቤት በመገንባት ሂደት ተጀምሯል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህሊና እርካታ የሚገኝበትና በኢትዮጵያውያን ባህል ውስጥ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው ብለዋል።
ይህ እሴት ባለፉት ዓመታት በሀገር ደረጃ እንዲጠናከር በማድረግ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ያለው ለሌለው እያካፈለ የመንግስት አቅም እየሆነ የመጣ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአረጋውያንንና የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስና አዳዲስ ቤቶችን በመገንባል፣ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን፣ በትምህርት መስክም የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና በበዓላት ወቅቶችም ድሆች የሚታገዙበት ሁኔታ እየተጠናከረ ነው ብለዋል።
የ2018 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጭቃ ቤት ይገነባ የነበረውን አሁን በተሻለ የግንባታ እቃዎች በክልሉ 640 አዳዲስ ቤቶች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
ለዚህ ስራ መሳካት ሁሉም በባለቤትነት እንዲሰራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፤ በሀገር ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወንድማማችነት ስሜት እንዲጎለብት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከመደጋገፍ አኳያ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ኹነት መሆኑን የገለፁት አቶ ፍቅሬ፤ በክረምት ወራት በሚከናወኑ የዘርፉ ስራዎች ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።
በክልሉ በ14 የስራ መስኮች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ከ2 ነጥበ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብን ያሳተፉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በዚህም በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚገመቱ ስራዎች በዚሁ ተግባር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የተቸገሩትን የመርዳት ባህል እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞን ደረጃ ከ240 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ የአረጋውያንንና የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስና የመስራት ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
235 አዳዲስ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ የቦንጋ ከተማ አስተዳደር፣ የካፋ ዞን፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ቤት የሚገነባላቸው አቶ ናስር ቃሲም በሰጡት አስተያየት፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረው አመስግነዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ39ኛ ዙር የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በደመቀ ሁኔታ እያካሄደ ይገኛል
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለ6ኛ ዙር በተለያዮ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በደማቅ ስነ-ስርአት በማስመረቅ ላይ ይገኛል
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ ድግሪ እና በስፔሻሊቲ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 479 ተማሪዎችን በዋናው ግቢ እያስመረቀ ነው