የተጎዱ የእርሻ መሬቶችን በተፈጥሯዊ ማዳበሪያ እንዲያገግሙ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው የቨርሚ ኮምፖስት ምርምር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የአጠቃቀም መመሪያና የፖሊሲ አቅጣጫ ለማዘጋጀት ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆን ተገለጸ
የቨርሚ ኮምፖስት የንጥረ ነገር ይዘትና ተገቢ የአጠቃቀም መጠንን ለመወሰን እየተካሄደ ያለው ምርምር፤ የተጎዱ የእርሻ መሬቶች እንዲያገግሙ ለማድረግና የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
ከፎሉር ፕሮጀክት ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ የተጎዱ የእርሻ መሬቶችን እንዲያገግሙ ማድረግ መሆኑን በፕላን ሚኒስቴር የፎሉር ፕሮጀክት የአካባቢና የማህበረሰብ ደህንነት ጥበቃ ኦፊሰር ዶ/ር በውቀቱ ኃይሌ ገልጸዋል።
ዶ/ር በውቀቱ እንደገለጹት፥ ኮምፖስትና ቨርሚ ኮምፖስት የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በአግባቡ መጠቀም የአፈር ለምነትን አሻሽሎ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
አርሶ አደሮች ቨርሚ ኮምፖስትን በባለሙያዎች የግንዛቤ ስልጠናና የግብዓት ድጋፍ በማግኘት ሲያዘጋጁ በውስጡ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች መጠን እና በአንድ ሄክታር መሬት የሚያስፈልገው የአጠቃቀም መጠን በትክክል እንዲወሰን ምርምር እየተካሄደበት መሆኑንም አስረድተዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሮች በየአካባቢው የተለያዩ የአዘገጃጀት ዘዴዎችና ግብዓቶችን እየተጠቀሙ በመሆናቸው ልምዶቻቸውን በማሰባሰብ ለመላው ሀገሪቱ በወጥነት የሚያገለግል የአጠቃቀም ምክረ ሐሳብ ለማዘጋጀት እየተሠራበት መሆኑን አብራርተዋል።
ከሀዋሳ፣ ጅማና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተውጣጡ የአፈር ተመራማሪዎች በሀገሪቱ ከተመረጡ 10 ወረዳዎች የቨርሚ ኮምፖስት ናሙናዎችን በመሰብሰብ የላቦራቶሪ ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የምርምር ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአጠቃቀም ምክረ ሐሳብ እንደሚዘጋጅ እና ለወደፊቱም የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ግብዓት እንደሚሆን ዶ/ር በውቀቱ ገልጸዋል።
ተግባሩ የአርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ ዘላቂ የግብርና ልማትን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
የተጎዱ የእርሻ መሬቶችን በተፈጥሯዊ ማዳበሪያ እንዲያገግሙ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው የቨርሚ ኮምፖስት ምርምር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የአጠቃቀም መመሪያና የፖሊሲ አቅጣጫ ለማዘጋጀት ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆን ተገለጸ

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ