በመጪው የትምህርት ዘመን የጉራጊኛ ቋንቋ የ4ኛ ክፍል የሙከራ ትምህርት ለማስጀመር የመጽሀፍ ዝግጅት መጠናቀቁን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
የዞኑ ትምህርት መምሪያ የ2018 የጉራጊኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት አፈጻጸም የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን የአስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊ እና የጉራጊኛ ቋንቋ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ገብሬ እንደገለፁት፤ ካለፉት አራት አመታት ከቅድመ አንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል በጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል።
ለውጤታማነቱም የቋንቋ መምህራን በየትምህርት ቤቱ እና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።
ከዚህም ባሻገርም በአፍ መፍቻ ቋንቋ መፅሃፍት በማዘጋጀት ለተማሪዎች የማዳረስ ስራ መስራቱንም አውስተዋል አቶ ደሳለኝ።
የጉራጊኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መሰጠቱ ለቋንቋው መልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያመላከቱት አቶ ደሳለኝ፤ ለዚህም የጉራጊኛ ቋንቋ ማህበረሰቡ እሴቱን፣ ባህሉን እና የዳኝነት ስርዓት የሚገልፅበት ነው ሲሉም አስረድተዋል።
በመጪው የትምህርት ዘመን የጉራጊኛ ቋንቋ የ4ኛ ክፍል የሙከራ ትምህርት ለማስጀመር የመጽሀፍት ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።
የቋንቋ መምህራን አሰልጥኖ የመቅጠር እና በጉራጊኛ የተፃፉ አጋዥ መፅሃፍት በየትምህርት ቤቶች ተደራሽ የማድረግ ስራ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።
ቋንቋውን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ የዞኑ አስተዳደር በርካታ ተግባራት እያከናወ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ አሁንም በተሻለ መልኩ ለማሳደግ ማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው በጉራጌ ዞን ከቅድመ አንደኛ እስከ 3ኛ ክፍል 96 ሺህ 7 መቶ 77 ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እየተማሩ ይገኛል ብለዋል።
የዞኑ አስተዳደር ለጉራጊኛ ቋንቋ እድገት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ አበረታች ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ መብራቴ፤ በቀጣይ ጉድለቶችን በተገቢው በመለየት መስራት ይጠበቃል ሲሉም አመላክተዋል።
በተለይም ከዚህ በፊት በጉራጊኛ ለደራሲያን የተዘጋጁ መፅሃፍት ወደ ቤተመፅሃፍት በማስገባት ህፃናት ባህላቸውና አካባቢያቸውን እንዲያውቁ በትኩረት መስራት ይጠበቃል በማለት አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ለሶስተኛ ክፍል በሙከራ ደረጃ ዞናዊ ምዘና እንደሚሰጥ የጠቆሙት አቶ መብራቴ ለዚህም ውጤታማነት በእውቀትም ሆነ በአመለካከት ትውልድን መቅረፅ ይገባል ነው ያሉት አቶ መብራቴ።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ለማካተት ከባለፉት አራት አመታት ጀምሮ በተሰሩ ስራዎች አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆኑን ገልፀዋል።
በተሰራው ስራም ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተሻለ መልኩ ትምህርት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸውም ጠቁመዋል።
በቀጣይም በተሻለ መልኩ በማስቀጠል በመማር ማስተማር ሂደት ላይ የተስተዋሉ ውስንነቶችን በተለይም የሰው ሃይል፣ አጋዥ መፅሃፍት እና ሌሎችንም የማሟላት ስራ ሊሰራ ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወ/ማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ39ኛ ዙር የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በደመቀ ሁኔታ እያካሄደ ይገኛል
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለ6ኛ ዙር በተለያዮ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በደማቅ ስነ-ስርአት በማስመረቅ ላይ ይገኛል
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ ድግሪ እና በስፔሻሊቲ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 479 ተማሪዎችን በዋናው ግቢ እያስመረቀ ነው