የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ አገልግሎት ያስገነባቸውን ዘመናዊ ኮምፕሌክሶችን አስመረቀ
ሀዋሳ: ሰኔ 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ አገልግሎት ያስገነባቸውን ዘመናዊ ኮምፕሌክሶችን የኢፌድሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በይፋ መርቀዋል።
ለአስተዳደር አገልግሎት፣ ለመምህራን መኖሪያ፣ ለተማሪዎች ካፍቴሪያና ለኤዲቶሪያል አገልግሎት የሚውሉ ህንጻዎች ናቸው በዛሬው እለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን የቆዬ ሲሆን ለዚህም ይረዳው ዘንድ ያስገነባቸውን የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ህንጻዎችን አስመርቋል።
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ፥ ለዩኒቨርሲቲው ታሪካዊ በሆነው እለት 4 ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን ጠቅሰው፥ ይህ የአመራር ቅብብሎሽ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም አሻራቸውን ያሳረፉና የቀደሙ አመራሮች ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
የተወሳሰበ ችግር የነበረባቸው ፕሮጀክቶች ለምረቃ መብቃታቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም የስራ አመራር ቦርድ የላቀ አስተዋጾ እንደነበረው አስታውሰዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌድሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤና ዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው አቶ አገኘሁ ተሻገር ዩኒቨርሲቲው ያሉበት ችግሮችን ለመፍታት ቦርዱ በ3 ኮሚቴዎች ተዋቅሮ ሲሰሳራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በተለይ የካፒታል ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን የተወሰደው እርምጃ በአብነትነት በማንሳት በዚህም ውጤታማ መሆን ስለ መቻሉም አብራርተዋል።
ከሁሉም በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤት ተገንብቶ መጠናቀቁ በስኬት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ተቋሙን ተወዳዳሪ ለማድረግ መስራት እንደሚጠይቅ በአጽንኦት ገልፀው፥ የቴክኖሎጂውን ዘመን የሚመጥኑ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት መሰራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ ያስተማራቸውን ከ700 በላይ ተማሪዎች በነገው ዕለት ያስመርቃል።
ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በጎፋ ዞን ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበጋ ማጠቃለያና የክረምት በጎ ስራ ማስጀመሪያ መረሃ-ግብር ተካሄደ
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ሀብት መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 1.5 ሚሊዬን ዜጎችን ለማሳተፍ መታቀዱ ተገለጸ