በሀገሪቱ ያለው 80 በመቶ ቡና ያረጀ በመሆኑ መታደስ እንደሚገባ ተጠቆመ

በሀገሪቱ ያለው 80 በመቶ ቡና ያረጀ በመሆኑ መታደስ እንደሚገባ ተጠቆመ

‎ሀዋሳ፡ ሰኔ 10/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ በፎሉር ፕሮጀክት አማካኝነት በቡና ንቅለ ተከላና ጉንደላ ዙሪያ በተሰጠ ስልጠና በሀገሪቱ ያለው 80 በመቶ የቡና ተክል ያረጀ በመሆኑ ሊታደስ እንደሚገባ ተመላክቷል።

‎በፕላን ሚኒስቴር የፎሉር ፕሮጀክት የአካባቢና የማህበረሰብ ደህንነት ጥበቃ ኦፊሰር በውቀቱ ኃይሌ(ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ በተደረገ ጥናት አብዛኛው የቡና ተክል ያረጀና ምርት የመስጠት አቅሙ የቀነሰ መሆኑ ታውቋል።

‎ዶ/ር በውቀቱ እንዳሉት፥ ያረጁ የቡና ተክሎችን በንቅለ ተከላና በጉንደላ ማደስ እና የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምር ጠቁመዋል።

‎የጌዴኦ ህዝብ በጥምር እርሻ የረጅም ዘመን ልምድ ያለው ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ ይህንን እውቀትና ግንዛቤ በማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑንም ገልጸዋል።

‎በደንና ቡና ልማት፣ በመሬት አያያዝ እና በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ ፕሮጀክቱ የሚያከናውነው ሥራ ሰፊ ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት ወረዳዎች ውስጥ የተጀመረው ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊስፋፋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎የኮቾሬ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ማሮ በበኩላቸው፥ ፎሉር ፕሮጀክት በወረዳው እስካሁን ከ230 ሄክታር በላይ የቆዩ የቡና ተክሎችን በማደስ ሥራ ላይ መሳተፉን ገልጸዋል።

‎አርሶ አደሮችም ቀደም ሲል ምርት የማይሰጡ የቆዩ የቡና ተክሎችን በማደስ ከግለሰብ እስከ ኩታ ገጠም ደረጃ የቡና ዕድሳት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

‎የኮቾሬ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የፎሉር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ግርማ ዘሪሁን እንደገለጹት፣ ከአምስት የፕሮጀክቱ ቀበሌያት ለተውጣጡ 500 አርሶ አደሮች የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የክህሎትና የተግባር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ከቦጂ፣ ረኮ እና አንጨቢ ቀበሌያት የተውጣጡ የስልጠናው ተሳታፊ አርሶ አደሮች አሰፋ ሺፈራውና ብርቱካን ተሰማ ከአያቶቻቸው የወረሱትን ወደ ዛፍነት የተቀየረ የቡና ተክል በማደስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ያገኙትንም እውቀት ለሌሎች አርሶ አደሮች ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን