ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻዉ ጣሰዉ በሶዶ ምርጫ ክልል ጎጊቲ 2 የመራጭነት ድምፅ ሰጡ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከማለዳዉ 12:00 ጀምሮ መራጩ ህዝብ ድምፁን መስጠት ጀምሯል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከተገኘባቸዉ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል አንዱ በሆነዉ በሶዶ ምርጫ ክልል የጎጊቲ 2 ምርጫ ጣቢያ መራጩ ህዝብ ከማለዳዉ 12:00 ጀምሮ በነቂስ በመዉጣት ይበጀኛል ላለዉ ድምፁን እየሰጠ ነዉ።
በዚህ ምርጫ ጣቢያ ድምፃቸዉን ከሰጡ መራጮች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንዳሻዉ ጣሰዉ አንዱ ናቸዉ።
የዘንድሮ ምርጫ ለየት የሚያደርገው የመራጮች ቁጥር በብዙ ሚሊየን መጨመሩ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህዝቡ ምርጫ ይጠቅመኛል የሚል እምነት ውስጡ ማደሩን ያረጋገጠበት እለት መሆኑን አውስተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ድምፃቸዉን ከሰጡ በኋላ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ምርጫ የፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ሉዓላዊነት በተግባር የሚገለጽበት እና ዴሞክራሲያዊ መሠረቶች በሕዝብ እጅ የሚረጋገጡበት ታላቅ ሀገራዊ ሁነት መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጫ ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን፣ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪም ራሱ ሕዝቡ መሆኑን በተግባር የሚታይበት ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑም ሁሉም የድምፅ መስጫ ካርድ የወሰደ መራጭ እስከ አመሻሽ 12:00 ባለዉ የመምረጫ ጊዜ መብቱን እንዲጠቀምና የዜግነት ግዴታዉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ።
በሌሎች የልማትና የሰላም ሂደቶች ላይም ህዝቡ የጀመረውን ተሳትፎ እንዲያስቀጥል አፅንኦት ሰተዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላምና በስኬት ተጠናቆ ሀገራችንን ወደ ላቀ ከፍታ እንዲያሻግራት መራጩ ህዝብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
#ደ.ሬ.ቴ.ድ

More Stories
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሌሞ 01 ምርጫ ክልል በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት እየተለጠፈ ይገኛል
ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ይፋ መደረግ ጀምሯል
በሀዲያ ዞን ሶሮ 02 ምርጫ ክልል ጃጁራ ከተማ አስተዳደር የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ይፋ መሆን ጀምሯል