‎ዜጎች የመራጭነት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ድምጽ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ

‎ዜጎች የመራጭነት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ድምጽ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ

‎ሀዋሳ: ግንቦት 24/208 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዜጎች የመራጭነት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ድምጽ እንዲሰጡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ጥሪ አስተላለፉ።

‎በሂደቱ እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ልምምድ የታየበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፥ በአርባምንጭ የምርጫ ክልል ጫሞ ካምፓስ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

‎7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፥ መላው ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥና የአገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የታየው ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ በእጅጉ ትምህርት የሚቀሰምበት መሆኑን አመላክተዋል።

‎ኢትዮጵያውያን ስልጣንን በካርድ፣ ያለ ምንም ግርግር ግጭትና ደም መፋሰስ መያዝ እንደሚቻል ያሳዩበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ሂደቱ ለአፍሪካ ብሎም ለአለም ትምህርት በመሆኑ የዲሞክራሲ ልምምዳችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥራትና በይዘት በእጅጉ እየተሻሻለ፣ የህዝብ ተሳትፎ ቁጥሩም እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

‎የዘንድሮ ምርጫ ካለፉት 6 ምርጫዎች በብዙ መለኪያዎች የተሻለ ከመሆኑም በላይ በክልሉ 22 የተፎካካሪ ፓርቲዎች፥ በ56 የምርጫ ክልል ሠላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና ገለልተኛ በሆነ መልኩ እየተፎካከሩ ነው ብለዋል።

‎የዲሞክራሲ መሠረቱ የነቃ የህዝብ ተሳትፎ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፥ ህዝቡ በሂደቱ የሚያሳየው ተነሳሽነት ኢትዮጵያ እየመረጠች ለመሆኑ ለአፍሪካም ሆነ ለሌላው ትምህርት የሠጠ ነው ብለዋል።

‎ዘጋቢ: ዘላለም ተስፋዬ