የጋብሪኤል ጄሱስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ

የጋብሪኤል ጄሱስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ

የአርሰናሉ አጥቂ ጋብሪኤል ጄሱስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አጠያያቂ ሆኗል።

በሰሜን ለንደኑ ክለብ ቤት የነበረው ቆይታ ሊጠናቀቅ የተቃረበ የሚመስል ሲሆን፣ አርሰናልም ተጫዋቹን ለመሸጥ ያለውን ዝግጁነት እያሳየ ይገኛል።

የቡድኑ አካል የሆነው ብራዚላዊው አጥቂ ጋብሪኤል ጄሱስ በክለቡ ያለው ቆይታ አደጋ ላይ መውደቁን ተከትሎ፣ በርካታ ክለቦች የ29 ዓመቱን ተጫዋች ለማስፈረም ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ።

አርሰናል ተጫዋቹን ለመልቀቅ በሮቹን ከፍቷል። እንደ ዘ አትሌቲክ ዘገባ ከሆነ፣ አርሰናል ለጄሱስ ከ18 ሚሊዮን ፓውንድ እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ የሚደርስ የዝውውር ክፍያ ይፈልጋል።

ይህ ዋጋ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ከማንቸስተር ሲቲ ወደ አርሰናል ሲመጣ ከነበረው ዋጋ አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ነው።

የአርሰናል ይህ ውሳኔ የመጣው ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ያለው ኮንትራት ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው መሆኑን ተከትሎ ነው።

ክለቡ በ2027 ኮንትራቱ ተጠናቆ ተጫዋቹ በነጻ ዝውውር ከመሄዱ በፊት፣ በዚህ ክረምት የተወሰነ ገቢ ለማግኘት ያለመ ነው።

ባለፈው የውድድር ዘመን በጉልበት ጉዳት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ውጭ የቆየው ጄሱስ፣ ከጉዳቱ በኋላ ጥሩ ብቃት ለማሳየት ቢጥርም በአርሰናል አጥቂዎች ተዋረድ ውስጥ ቦታው እየጠበበ መጥቷል።

አጥቂው ታህሳስ ወር ላይ ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላ በ27 ጨዋታዎች 6 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

እንደ ቪክቶር ጂዮከሬስ እና ካይ ሃቨርትዝ ያሉ ተጫዋቾች መምጣት፣ ጄሱስን ከቋሚ አሰላለፍ ወደ ተጠባባቂነት እንዲሸጋገር አድርገውታል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ መጀመር የቻለው ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው።

ጋብሪኤል ጄሱስ ከአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ጋር በማንቸስተር ሲቲ የነበረውን የቆይታ ጊዜ በመቀጠል፣ በ2022 ወደ አርሰናል አምርቶ ቡድኑ ለፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ተፎካካሪ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

በለንደን በቆየባቸው አራት ዓመታት በ123 ጨዋታዎች 32 ግቦችን በማስቆጠር እና 22 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ለክለቡ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ምንም እንኳን ጄሱስ በቅርቡ “በአርሰናል ያልጨረስኩት ስራ አለ፣ መውጣት አልፈልግም” በማለት በክለቡ የመቆየት ፍላጎቱን የገለጸ ቢሆንም፣ ወደፊት ወደ ልጅነት ክለቡ ፓልሜራስ የመመለስ ህልሙን አልሸሸገም።

አሁን የሚጠበቀው ጥያቄ አርሰናል በጄሱስ የተገመተውን የ20 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ የሚከፍል ክለብ አግኝቶ ተጫዋቹን ይሸጥ ይሆን ወይስ ጄሱስ በክለቡ ቆይቶ ለቦታው ይታገላል? የሚለው ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ