ከቪዬራ እስከ ኦዴጋርድ
እግር ኳስ ጊዜን የሚያቆም፣ ታሪክን ደግሞ የሚደግም ጥበብ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያለፈው ታሪክ እና የአሁኑ እውነት በትልቅ ድልድይ ይገናኛሉ።
ከለንደኑ ሃይበሪ ስታዲየም እስከ ዘመናዊው ኤምሬትስ፤ ከፈረንሳዊው ብረት አውታር ፓትሪክ ቪዬራ እስከ ኖርዌያዊው የጥበብ መሃንዲስ ማርቲን ኦዴጋርድ።
ከ2004ቱ የማይደፈሩት ስብስብ እስከ 2026ቱ አዲሱ የአርሰናል ትውልድ።
መድፈኞቹ የሁለት አስርት ዓመታት የዋንጫ ናፍቆታቸውን ለመስበር ሲገሰግሱ፣ የታሪክ ማህደር እንዲህ ይገለጣል…
እ.ኤ.አ በ2004 አርሰናል በለንደን ሰማይ ስር ታሪክ ሰራ። በፓትሪክ ቪዬራ መሪነት፣ በአርሰን ቬንገር ጥበበኛነት፣ ክለቡ ያለ ምንም ሽንፈት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አነሳ።
ያ የሃይበሪ ስታዲየም ዘመን ነበር። ቪዬራ በሜዳው መሃል ላይ እንደ አጥር የቆመ፣ የተጋጣሚን መስመር የሚያፈርስ፣ ለጠላት የማይበገር መሪ ነበር። ያ ቡድን በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ አስቀምጦ አለፈ።
ነገር ግን ከሃይበሪ ወደ ኤምሬትስ የተደረገው ጉዞ ለክለቡ ቀላል አልነበረም። ስታዲየም መቀየር ብቻ ሳይሆን፤ የክለቡ ማንነት እና የድል ረሃብም አብሮ የተፈተነበት ረጅም የሃያ ዓመታት ጉዞ ተጀመረ።
ቪዬራ ለቆ ከወጣ በኋላ አርሰናል በርካታ መሪዎችን አጥቷል። ከቲየሪ ኦነሪ እስከ ሴስክ ፋብሪጋዝ፣ ከሮቢን ቫን ፐርሲ እስከ ሎራን ኮሲየልኒ ያሉት መሪዎች የቪዬራን ትልቅ ጫማ መሙላት አልቻሉም ነበር።
ኤምሬትስ ስታዲየም የናፍቆት እና የብስጭት ምድር ሆና አመታትን አሳለፈች።
ነገር ግን ታሪክ የሚቀየረው በትክክለኛ መሪዎች እጅ ነው። የቀድሞው የአርሰናል አማካኝ ሚኬል አርቴታ የቡድኑን መንበር ሲረከብ መጀመሪያ የፈለገው የጠፋውን የክለቡን “ዲ ኤን ኤ” (DNA) እና የሜዳ ላይ መሪ መመለስ ነበር። እዚያ ጋ ነው እንግዲህ ታሪክ ማርቲን ኦዴጋርድን ወደ ለንደን ያመጣው።
ማርቲን ኦዴጋርድ በ15 ዓመቱ “የዓለም እግር ኳስ ተአምር” ተብሎ ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለ ቢሆንም በሳንቲያጎ በርናባው ግን ክንፉን መዘርጋት አልቻለም ነበር።
ብዙዎች “ኦዴጋርድ መክኗል” ብለው ደምድመውለት ነበር። አርቴታ ግን የዚህን ወጣት የውስጥ እሳት ተመለከተ።
ዛሬ በ2026 ማርቲን ኦዴጋርድ የአርሰናል መቶ አለቃ ብቻ አይደለም፤ እርሱ የቡድኑ ልብ እና አእምሮ ነው።
የቪዬራ መሪነት በጉልበት እና በቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ነበር።
የኦዴጋርድ መሪነት ደግሞ በጥበብ፣ በክህሎት እና ቡድኑን በማስተሳሰር ላይ የተገነባ ነው።
ኦዴጋርድ ሜዳ ላይ ሲጫወት እንደ ቼዝ ተጫዋች ነው፤ ከተጋጣሚ ሶስት እና አራት እርምጃዎችን ቀድሞ ያስባል። እሱ በሚያማምሩ እግሮቹ ኳስን ሲያዘውር፣ የኤምሬትስ ስታዲየም በደስታ ይናወጣል።
ከ2004 እስከ 2026 ሃያ ሁለት ዓመታት አለፉ። አርሰናል አሁን የደረሰበት የብቃት ደረጃ የቪዬራ ዘመን የነበረውን ፍርሃት አልባነት ያሳየናል።
ቪዬራ በጉልበቱ ያስከበረውን የሰሜን ለንደን ክብር ዛሬ ኦዴጋርድ በጥበቡ እያደሰው ይገኛል።
ያኔ ከ22 ዓመታት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ፓትሪክ ቪዬራ ነበር ለመድፈኞቹ የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ያነሳላቸው ዛሬ ደግሞ ማርቲን ኦዴጋርድ ባለተራ ሆኗል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
መሐመድ ሳላህ ከአንፊልድ ሲሰናበት
“ አርሰናልን መቀላቀሌ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር ” ዴክላን ራይስ
ብሩኖ ፈርናንዴዝ የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ!