መሐመድ ሳላህ ከአንፊልድ ሲሰናበት
አንዳንድ ታሪኮች የሚለኩት በሰከንዶች እና በደቂቃዎች ነው፤ ሌሎቹ ደግሞ በዋንጫዎች እና በቁጥሮች።
ነገር ግን መሐመድ ሳላህ በሊቨርፑል የጻፈው ታሪክ ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነው። እሱ የታሪክ መጽሐፍትን መልሶ የጻፈ፣ የአንድን ታላቅ ክለብ ማንነት የቀየረ እና በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የማይደበዝዝ አሻራ ጥሎ ያለፈ ‘ድንቅ ተጫዋች’ ነው።
ዛሬ እሁድ፣ በአንፊልድ ስታዲየም የመጨረሻው የመለያያው ሰዓት ደርሷል። ሳላህ ከሊቨርፑል ደጋፊዎች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ አይን ለአይን ሊገጣጠም ነው። ይህ ስንብት ግን ተራ ስንብት አይደለም፤ የአንድ ዘመን ማክተሚያ እንጂ!
ወደ ኋላ በ2017 ዓ.ም እንመለስ። ሊቨርፑል ይህንን ቀጭን ግብፃዊ ከሮማ በ34 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስፈርም፣ የለንደኑ ቼልሲ ውድቀቱን ያስታወሱ ብዙዎች ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። ‘በመርሲሳይድ ምድር ምን ሊሰራ ይችላል?’ አሉ።
ነገር ግን በናግሪግ ገጠራማ መንደር የተወለደው ሳላህ፣ የሰዎችን ጥርጣሬ ወደ እምነት ለመቀየር ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም።
የመጀመሪያ ጨዋታውን በዋትፎርድ ሜዳ ሲያደርግ፣ በዕረፍት ሰዓት ሊቨርፑል 2 ለ 1 እየተመራ ነበር። የክለቡ ታላቅ መሪ የነበሩት የርገን ክሎፕ ወደ ሳላህ ጠጋ ብለው “እንኳን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በሰላም መጣህ” አሉት።
በሁለተኛው አጋማሽ ሳላህ ግብ አስቆጠረ። ከዚያ ቀን ጀምሮ የሳላህ፣ የሳዲዮ ማኔ እና የሮቤርቶ ፊርሚኖ ጥምረት በአውሮፓ ምድር ፍርሃትን የሚዘራ፣ የተቃራኒ ተከላካዮችን ቅስማቸውን የሚሰብር አስፈሪ ጥምረት ሆነ።
የማንቸስተር ሲቲው አለቃ ፔፕ ጋርዲዮላ በአንድ ወቅት ስለነሱ ሲናገር “ያስፈሩኛል፣ እነሱ በጣም አደገኛ ናቸው” ለማለት ተገደው ነበር።
በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ ‘ጎል እና አሲስት’ ትልቁ የነጻነት መገበያያ ገንዘብ ከሆነ፣ ሳላህ በሊቨርፑል ታሪክ ውስጥ እጅግ ባለጸጋው ሰው ነው።
ለቀያዮቹ ባደረጋቸው ጨዋታዎች 257 ጎሎችን አስቆጥሮ 119 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። ይህ ማለት በየ 94 ደቂቃው አንድ የጎል ተሳትፎ ነበረው ማለት ነው! አስገራሚ፣ አስደናቂ፣ ተአምረኛ!
እንደ ሰር ኬኒ ዳግሊሽ፣ ሮቢ ፋውለር እና ስቲቨን ጄራርድ ያሉ የክለቡን ባለውለታዎች በጎል ብዛት አስከንድቷል።
በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ደግሞ ለአንድ ክለብ ከፍተኛ የጎል ተሳትፎ (283) በማድረግ ረገድ ከሳላህ በላይ ማንም የለም።
በሊቨርፑል ታሪክ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አግቢ ኢያን ረሽ ስለሳላህ ሲናገር “መሐመድ የሊቨርፑል ሌጀንድ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር፣ ነገሩን ግን ወደ ሌላ ከፍታ ወሰደው። አንድ ቀን እኔ ያስቆጠርኩትን የጎል ብዛት ማመን አቅቶት ‘ለመሆኑ በልምምድ ወቅት የምታስቆጥረውን ጎል ትቆጥር ነበር?’ ብሎ ቀለደብኝ” ይላሉ። ስለራሱስ ምን ይል ይሆን?
ይህ ስኬት ግን በዕድል የመጣ አይደለም። ሳላህ ለእግር ኳስ ህይወቱ ሙሉ አካሉን እና ነፍሱን የሰጠ ባለሞያ ነው።
ቨርጅል ቫን ዳይክ እንደተናገረው እሱ “በአርአያነት የሚመራ መሪ” ነው።
በእርግጥ በመጨረሻው የውድድር ዘመን ከአዲሱ አሰልጣኝ አርነ ስሎት ጋር የነበረው ግንኙነት መሻከር እና በሌድስ ዩናይትድ ጨዋታ ላይ በተቀያሪ ወንበር በመቀመጡ መናደዱ የፍጻሜው መጀመሪያ ነበር።
ኮንትራቱን ከአንድ ዓመት ቀድሞ ለማቋረጥ የተስማማውም ለዚህ ነው።
ነገር ግን ሳላህ የጎል ማሽን ብቻ አይደለም፤ ፍጹም ሰው ነው።
ባለፈው ክረምት የቡድን አጋሩ ዲዮጎ ጆታ በድንገት ሲያርፍ፣ በአንፊልድ ስታዲየም ፊት ለፊት ስቅስቅ ብሎ ሲያለቅስ ያየነው ሳላህ፣ ከታላቅነቱ በስተጀርባ ትልቅ የሰው ልጅ ልብ እንዳለው ያሳየበት አጋጣሚ ነበር።
ያለፈው የ2024-25 የውድድር ዘመን በታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም የሚጻፍ ነው። ሳላህ ሊቨርፑልን መርቶ 20ኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ በሊጉ ከፍተኛ ጎል እና አሲስት በመያዝ የእንግሊዝ እግር ኳስን አምበርክኮ ነበር።
እነዚህን አጋጣሚዎችንስ ማን ሊረሳው ይችላል? በ2019 በማድሪድ ቶተንሃም ላይ ያስቆጠራትን የሁለተኛ ደቂቃ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል፣ በኤቨርተን ላይ አስቆጥሮ የፑሽካሽ ሽልማት ያገኘበትን ያችን ድንቅ ጎል፣ በማንቸስተር ሲቲ ተከላካዮች መሃል እንደ እባብ ተሽሎክልኮ ያስቆጠራትን ያቺን አስማታዊ ጎል እና ሌላም አስደናቂ ክህሎቶች።
የማንቸስተር ሲቲው ተከላካይ አይመሪክ ላፖርት ዛሬም ድረስ ያቺን ቅፅበት በቅዠት ያስታውሳታል “ቦታዋ ጥቂት ሴንቲሜትሮች ብቻ ነበረች፣ ግን በደካማ እግሩ አስቆጠራት። እሱ እኛን በገጠመ ቁጥር ሁሌም በእኛ ላይ ይበረታ ነበር” ይላል።
ጎል አስቆጥሮ ማሊያውን አውልቆ ሲደሰት፣ ወይም በሜዳው ላይ ተንበርክኮ ወደ መሬት ሲሰግድ የነበሩት ምስሎች በአንፊልድ ለዘላለም ይኖራሉ።
ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ሳላህን ከታላቁ ስቲቨን ጄራርድ ጋር እኩል “ቁጥር አንድ የክለቡ ሌጀንድ” ማለቱ ያለምክንያት አይደለም።
አሁን ሁሉም ነገር ሊያበቃ ነው። በአሁኑ ሰዓት ሳላህ በቀጣይ የት እንደሚያመራ ባይታወቅም፣ ዛሬ ከብሬንትፎርድ ጋር የሚደረገው ጨዋታ የዚህ ታላቅ ታሪክ የመጨረሻ ገጽ ይሆናል።
ሙሉ ዘጠኝ ዓመታት በክብር፣ በዋንጫ፣ በደስታ እና በንጉሳዊ ግርማ።
የርገን ክሎፕ እንዳሉት “እሱ ለክለቡ ፍጹም ተጫዋች ነበር፣ ክለቡም ለእሱ ፍጹም ቦታ ነበር። አንድ ሰው ሲመጣ ሰዎች ምን ያስባሉ የሚለው አይደለም ዋናው፤ ትልቁ ነገር ሲወጣ ምን ያስባሉ የሚለው ነው!”
ዛሬ አንፊልድ ተነስቶ ያጨበጭባል፤ ታላቁ የኮፕ ስታንድ የሳላህን ሞዛይክ ምስል ወደ ላይ ያነሳል።
መሐመድ ሳላህ—የሊቨርፑል የዘላለም ንጉስ፣ ታሪክ ስላንተ በክብር ይናገራል!
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
“ አርሰናልን መቀላቀሌ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር ” ዴክላን ራይስ
ብሩኖ ፈርናንዴዝ የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ!
“የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መባል ስሜቱ የማይታመን ነው!”— ሚኬል አርቴታ