“ አርሰናልን መቀላቀሌ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር ” ዴክላን ራይስ

“ አርሰናልን መቀላቀሌ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር ” ዴክላን ራይስ

በኳስ ሜዳ ላይ ብልህ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የአሸናፊነት ሚስጥር ነው።

አንዳንድ ውሳኔዎች ደግሞ የህይወትን ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ይቀይራሉ።

እንግሊዛዊው አማካይ ዴክላን ራይስ ወደ ሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ቤት ያደረገው ዝውውር ልክ እንደዚሁ ነበር።

ተጫዋቹ አርሰናልን ለመቀላቀል የወሰነው ውሳኔ “ፍፁም ትክክለኛ” እንደነበር በልበ ሙሉነት ተናግሯል።

ከዚህ ውሳኔ ጀርባ ደግሞ የአንድ ስፔናዊ ታክቲሺያን የማሳመን ጥበብ አለበት።

የቀድሞው የዌስትሃም አምበል ዴክላን ራይስ፥ መድፈኞቹን ከመቀላቀሉ በፊት ከሌሎች ታላላቅ ክለቦች የቀረቡለትን በርካታ አማራጮች ወደ ጎን በመተው ነበር መድፈኞቹን የመረጠው።

ታዲያ ለዚህ ምርጫው ዋነኛው ምክንያት የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እንደሆነ ራይስ በግልጽ መስክሯል።

ከአሰልጣኙ ጋር ስላደረገው የመጀመሪያ ንግግር ትዝታውን ያጋራው አማካዩ፥ “ሚኬል ስለ እግር ኳስ የሚናገርበት እና የክለቡን የወደፊት እቅድ የሚገልፅበት መንገድ ፍጹም የተለየና ማራኪ ነው” ሲል የአርቴታን ልዩ የመሳብ አቅም ገልጿል።

በእግር ኳስ አለም ብዙ ቃል ይገባል፤ በተግባር የሚታየው ግን ጥቂቱ ነው።

ራይስን እጅግ ያስደነቀውም ይኸው የመሬት ላይ እውነታ ነው።

“አርቴታ በመጀመሪያው ቀን የተናገራቸው እና ቃል የገባልኝ ነገሮች በሙሉ ዛሬ ወደ ተግባር ተቀይረው እውነት ሆነዋል። ይህ ደግሞ እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ነው” ሲል ለስፔናዊው አሰልጣኝ ያለውን አክብሮት አሳይቷል።

አንድ ተጫዋች በአሰልጣኙ ላይ ፍጹም እምነት ሲኖረው በሜዳ ላይ ያለው ብቃት በእጥፍ ይጨምራል።

ራይስም ይህንን እውነት ሲያረጋግጥ “ወደ አርሰናል መዘዋወሬ ፍፁም ትክክለኛ ውሳኔ ነበር። ሌሎች በርካታ አማራጮች ነበሩኝ፤ ነገር ግን ከአርቴታ ጋር ከተነጋገርን በኋላ እነዚያ አማራጮች በሙሉ ከአእምሮዬ ጠፉ” ይላል ራይስ።

ራይስ አክሎም “በእግር ኳስ ህይወቴ በአንድ ጨዋታ እና በአሰልጣኝ ላይ እንደዚህ አይነት ጠንካራ እምነት አድሮብኝ አያውቅም” በሏል።

ይህ የራይስ ምስክርነት የሚያሳየው አርሰናል በአሁኑ ሰዓት ታላላቅ ኮከቦችን በገንዘብ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ በጨዋታ ፍልስፍና እና በፕሮጀክት ጥራት ጭምር መሳብ የቻለበት የዕድገት ማማ ላይ መድረሱን ነው።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ