“የቦርንማውዝ ትልቁ ደጋፊ እኔው ነኝ!” – ሚኬል አርቴታ

“የቦርንማውዝ ትልቁ ደጋፊ እኔው ነኝ!” – ሚኬል አርቴታ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዚህ የውድድር ዘመን ማጠቃለያ ድራማዊነቱ እያየለ መጥቷል።

ትናንት ምሽት አርሰናል በርንሊን 1 ለ 0 አሸንፎ የዋንጫው መድረሻ ደጃፍ ላይ ቆሟል።

አሁን መድፈኞቹ የሊጉን ዘውድ ለመድፋት የሚቀራቸው አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ማክሰኞ ምሽት በቦርንማውዝ ሜዳ ላይ ነጥብ እንዲጥል መጸለይ!

የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታም ይሄንን አጋጣሚ በጉጉት እየጠበቁ ነው።

በዛሬው ዕለት ከማንኛውም የቦርንማውዝ ደጋፊ በላይ ለክለቡ እንደሚጮህ በፈገግታ ገልፀዋል።

ነገሩን ይበልጥ ማራኪ የሚያደርገው ደግሞ የቦርንማውዙ አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ እና ሚኬል አርቴታ በባስክ ምድር በአንድ የህጻናት ቡድን ውስጥ አብረው ያደጉና የተጫወቱ የልጅነት ጓደኛሞች መሆናቸው ነው።

ባለፈው ሳምንት የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ አርሰናልን እንዲያቆምላቸው ለዌስትሃም ደጋፊነታቸውን ገልጸው ነበር።

ዛሬ ደግሞ ተራው የአርቴታ ነው። በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች ውስጥ ረጅሙን የ16 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ እያደረገ ለሚገኘው ቦርንማውዝ አርቴታ ሙሉ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

“የቦርንማውዝ የዘመናት ትልቁ ደጋፊ እኔ ነኝ! ለአንዶኒ፣ ለተጫዋቾቹ እና ለደጋፊዎቻቸው ዛሬ ሁላችንም የቦርንማውዝ ደጋፊዎች ነን። ምክንያቱም ዛሬ እነሱ የሚያመጡት ውጤት ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን” ሲሉ ሚኬል አርቴታ ተናግረዋል።

አርቴታ ለጓደኛቸው ለኢራኦላ ምንም አይነት የቴክኒክ ምክር መላክ እንደማያስፈልገው ይናገራሉ።

ምክንያቱም ኢራኦላ በቦርንማውዝ ላይ ያመጣው ለውጥ እና አሁን ቡድኑ ያለው የወኔ ስሜት ለፈተናው በቂ መሆኑን ያምናሉ።

“ትናንት በርንሊዎች እንዴት እንደተጫወቱ፣ ያሳዩትን መንፈስ እና ጨዋታውን እንዴት እንዳከበዱት ስታዩ ቦርንማውዝ ደግሞ ዛሬ ምን ያህል ሊከብድ እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ” ብለዋል አርቴታ።

ነገር ግን አርቴታ ጨዋታውን ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር አብሮ አያዩትም። በቤታቸው ሆነው ከቤተሰባቸው ጋር በቴሌቪዥን ለመከታተል ወስነዋል።

ሆኖም የጨዋታው አስደናቂ ውጥረት እስከመጨረሻው ለመመልከት እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልፅዋል።

“ቴሌቪዥኑ ፊት እቀመጣለሁ፤ ነገር ግን ውጥረት የበዛበትን ያንን ጨዋታ እስከመጨረሻው ለማየት ምን ያህል አቅም እንደሚኖረኝ አላውቅም። እውነታው ይሄ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

እግር ኳስ ውበቱ እዚህ ላይ ነው! የሁለት የልጅነት ጓደኛሞች ትስስር እና የታላላቅ ክለቦች የዋንጫ ፉክክር በአንድ ምሽት ይገናኛሉ።

ሳምንታትን ሙሉ ያለመሸነፍ ጉዞ ላይ ያለው ቦርንማውዝ፣ ዛሬ ለራሱ ክብር ሲል ማንቸስተር ሲቲን ካቆመ የለንደኑ ቀይ ክፍል (አርሰናል) የረሃብ ዘመኑን የሚያበቃበት ታሪካዊ ምሽት ይሆናል።

ለመሆኑ ውድ የገጻችን ተከታዮች፤ ዛሬ ምሽት ቦርንማውዝ የሲቲን ግስጋሴ ገትቶ ለአርሰናል የዋንጫ መንገድ ይከፍታል ወይስ ሲቲ የተለመደውን የጭካኔ ጉዞውን ይቀጥላል? ግምታችሁን በኮሜንት አጋሩን!

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ