“የቤት ስራችንን ለመጨረስ ተቃርበናል” — ሚኬል አርቴታ

“የቤት ስራችንን ለመጨረስ ተቃርበናል” — ሚኬል አርቴታ



የአርሰናሉ አለቃ ሚኬል አርቴታ ዛሬ ምሽት በኤምሬትስ ስታዲየም ከበርንሌይ ጋር ለሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ ተጫዋቾቻቸው የተፈጠረላቸውን ወርቃማ ዕድል በእጃቸው እንዲያስገቡ አጥብቀው አሳስበዋል።

ይህ ጨዋታ መድፈኞቹ ላለፉት 22 ዓመታት በናፍቆት ለጠበቁት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ “የመጨረሻውን ምዕራፍ” እንዲያጠናቅቁ የሚያስችላቸው ነው።



አርሰናል የምሽቱን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ በ 5 ነጥቦች ልዩነት ይመራል።



ማንቸስተር ሲቲ በቦርንማውዝ የሚሸነፍ ወይም አቻ የሚወጣ ከሆነ አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ይሆናል!



ሚኬል አርቴታ ስለ ዋንጫ ጉዟቸው እንዳሉት “ባለፉት አራት ዓመታት በገነባነው ወጥነት፣ በሰበሰብነው ነጥብና ባስመዘገብነው ድል አሁን ጥቂት ትልልቅ ዋንጫዎች በእጃችን መግባት ነበረባቸው። ይህ ዓይነቱ ፈተና የሚገጥመው በዚህ ሊግ ብቻ ነው፤ ግን ይሄ ይበልጥ ጠንካራ እንድንሆን ያደርገናል። አሁን የቀረን ስራችንን ማጠናቀቅ ብቻ ነው፤ በቀጣዮቹ ሶስት ቀናትም ትልቁ ዕድል በእጃችን ላይ ይገኛል” በለዋል።



ሚኬል አርቴታ አክለውም ይህ ስኬት ከ2019 ጀምሮ የባለቤቶቹ ፍላጎት፣ የደጋፊዎቹ እልህ፣ የተጫዋቾችና የክለቡ ሰራተኞች ጥረት የተደመረበት የጋራ ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።



“ሁሉም ነገር በአንድ መስመር ሊሰለፍ ይገባል፤ ምክንያቱም የዚህ ሊግ ደረጃ እጅግ በጣም ከባድ ነው” ያሉት ስፔናዊው አሰልጣኝ “አሁን ግን ከምንጊዜውም በላይ ወደ ዋንጫው ቀርበናል” ሲሉ ተናግረዋል።



አርቴታ ስለዛሬው ምሽት ተጋጣሚያቸው በሰጡት አስተያየት “ማድረግ ያለብን ብቸኛው ነገር ከተጋጣሚያችን የተሻልን መሆን መቻላችንን ማረጋገጥ ብቻ ነው። በርንሌይ ከአስቶንቪላ ጋር ሲጫወት ያየ ሰው ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ያውቃል። አሁን የማስበው ስለ አሁኑ ጊዜ ብቻ ነው፤ ትኩረቴ ሁሉ በርንሌይ ላይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።



አርሰናል ባለፉት ሶስት ዓመታት በሁለተኝነት ማጠናቀቁ ያመጣበት ቁስል ለዘንድሮው ስኬት ትልቅ ነዳጅ ሆኖታል።

መድፈኞቹ ታሪክ ይሰራሉ ወይስ ሲቲ በመጨረሻው ሰዓት ዋንጫውን ይነጥቃል?

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ