«ራይስ አርሰናልን መምረጡ ያበሳጨኛል» ብሩኖ ፈርናንዴዝ

«ራይስ አርሰናልን መምረጡ ያበሳጨኛል» ብሩኖ ፈርናንዴዝ

የዘንድሮው የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማጠናቀቂያ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት፣ ከሜዳው ውጭ ያሉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ፉክክር አሁንም መነጋገሪያነቱ አልበረደም።

ሽልማቱን የ28 ድምጽ ልዩነት (45 በመቶውን ጠቅላላ ድምጽ በመውሰድ) ያሸነፈው የማንችስተር ዩናይትድ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ፣ ከቅርብ ተፎካካሪው ዴክላን ራይስ ጋር ስላለው ግንኙነት እና ስላለው የተጫዋችነት አቅም ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ብሩኖ ፈርናንዴዝ ከጆኤል ቤያ ቲቪ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ ከዴክላን ራይስ ጋር ያላቸው ወዳጅነት የጀመረው እ.ኤ.አ በ2023 ክረምት በፖርቱጋል አልጋርቭ አካባቢ በሚገኘው ‘አፕክስ ፉትቦል ፐርፎርማንስ’ የልምምድ ካምፕ በጋራ ሲሰለጥኑ እንደነበር አስታውሷል።

ፈርናንዴዝ ስለ ዴክላን ራይስ ሲናገር”በመጀመሪያ ደረጃ ለስብዕናው ትልቅ አክብሮት አለኝ። ከአልጋርቭ የልምምድ ጊዜያችን ጀምሮ በቅርብ አውቀዋለሁ። በዌስትሃም እያለም ቢሆን ያለውን ድንቅ ብቃት ሁላችንም የምናውቀው ነበር። እኔ ሁልጊዜም ቢሆን ራይስ ለማንችስተር ዩናይትድ ፍጹም ተስማሚ ተጫዋች ነው ብዬ አስብ ነበር። በመጨረሻም አርሰናልን ለመቀላቀል ሲወስን ትልቅ ሃዘን ነው የተሰማኝ” ሲል ተናግሯል።

ፖርቱጋላዊው አማካይ አክሎም፣ በማንችስተር ዩናይትድ በኩል ተጫዋቹን ለማስፈረም የተከፈተ ዕድል ስለመኖሩ በወቅቱ የሚያውቀው ነገር ባይኖርም፣ ራይስ በባህሪው፣ በባለሙያነቱና በሜዳ ላይ ስብዕናው ለኦልድ ትራፎርዱ ክለብ ፍጹም ተመራጭ እንደነበር አልሸሸገም።

ብሩኖ ስለ ብቃታቸው ልዩነት ሲያስረዳ”እኛ የምንጫወትበት ቦታና የአጨዋወት ስልታችን የተለያየ ነው። እሱ እንደ እኔ ብዙ አሲስት ማድረግ ወይም ጎል ማስቆጠር አይጠበቅበትም፤ ምክንያቱም አርሰናል ከእሱ የሚፈልገው የተለየ ሚና አለው። ስለዚህ ተጫዋቾቹን ማወዳደር አንችልም። ነገር ግን ዴክላን ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ ካሉት ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው” በማለት አስረድቷል።

ብሩኖ ፈርናንዴዝ ንግግሩን ሲቋጭ፣ ሽልማቱን በማሸነፉ ደስተኛ ቢሆንም ራይስም ቢያሸንፈው ሙሉ በሙሉ የሚገባው እንደነበር ገልጾ፣ “በውድድር ዘመን ምርጫ ሲደረግ ቁጥሮች (የጎል እና አሲስት መረጃዎች) ከፍተኛ ሚዛን ይደፋሉ። እኔ ድንቅ የውድድር ዘመን አሳልፌያለሁ። ዴክላን ደግሞ በሜዳው የኋላ ክፍል ስለሚጫወት እነኝህን ቁጥሮች ማግኘት ይከብደዋል። እሱ አሁንም ድንቅ ተጫዋች ነው፤ ሽልማቱን ቢያገኝ ኖሮ ልክ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሲደርስ የእንኳን አደረሰህ መልዕክት እንደላክሁለት ሁሉ አሁንም ቀድሜ ደስ አለኝ እለው ነበር” ብሏል።

የዘንድሮው የእግርኳስ ፀሐፊዎች ማህበር ሽልማት በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል።

ዴክላን ራይስ አርሰናልን ከ2004 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ በትከሻው ተሸክሞ እያገዘ ባለበትና አስደናቂ ዓመት እያሳለፈ በሚገኝበት ወቅት ሽልማቱ ለብሩኖ መሰጠቱ ያላስደሰታቸው አልጠፉም።

ሆኖም ብሩኖ ፈርናንዴዝ ዘንድሮ 8 ጎሎችን አስቆጥሮ፣ በሊጉ የአንድ የውድድር ዘመን የከፍተኛ አሲስት (20) ታሪካዊ ክብረወሰን ከያዙት ቲየሪ ኦነሪ እና ኬቪን ደ ብሩይነ በአንድ አሲስት ብቻ አንሶ (19 አሲስቶች ላይ) ይገኛል።

ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ