“ዳኛው ትክክለኛ ውሳኔ በመወሰኑ ደስተኛ ነኝ” ሚኬል አርቴታ
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ፉክክሩ እያየለ በመጣበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የመድፈኞቹ አለቃ ሚኬል አርቴታ በዌስትሀም ዩናይትድ እና በአርሰናል ጨዋታ ላይ የታየውን የቫር (VAR) ውሳኔ በመደገፍ ፅኑ አቋማቸውን በድጋሚ አንፀባርቀዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የዌስትሀም ዩናይትድ ግብ በቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) መሻሩን ተከትሎ ብዙዎች አስተያየታቸውን ሲሰነዝሩ ቢቆዩም፣ አርቴታ ግን ውሳኔው ፍጹም ተገቢ እንደነበር በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
አሰልጣኙ፣ የእግር ኳስን ህግጋትና ውስጣዊ ባህሪ ለሚያውቅ ሰው ውሳኔው አነጋጋሪ ሊሆን እንደማይገባ ጠቁመዋል። “እግር ኳስ ተጫውቶ ያለፈ ሁሉ የዚህን ውሳኔ ባህሪ ይረዳል፤ በመጨረሻም ትክክለኛው ውሳኔ በመወሰኑ ደስተኛ ነኝ” ሲሉ የዳኞቹን ውሳኔ አሞካሽተዋል።
አርሰናል የፊታችን ሰኞ ከበርንሌይ ጋር ወሳኝ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።
ይህን ጨዋታ ካሸነፉ ማክሰኞ ዕለት ተቀናቃኛቸው ማንችስተር ሲቲ ከበርንማውዝ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ከተጫዋቾቻቸው ጋር በመሆን የመከታተል እቅድ እንዳላቸው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ አርቴታ ምላሽ ሲሰጡ “ማንችስተር ሲቲን ከመጠበቅ ይልቅ በርንሌይን ማሸነፍ ላይ ብቻ እናተኩራለን” ብለዋል፡፡
የሰሜን ለንደኑ ክለብ የሊጉን ዋንጫ ዕጣ ፈንታ በሌሎች ክለቦች ውጤት ላይ ሳይሆን በራሱ ጥረት ለመወሰን እንደሚፈልግ አርቴታ አስምረውበታል።
ሚኬል አርቴታ ካለፈው ዓመት ስህተቱ የተማረ ይመስላል። አሁን ላይ ትኩረቱ በዳኞች ውሳኔ ወይም በሌሎች ክለቦች ውጤት ላይ ሳይሆን፣ በገዛ ቡድኑ ብቃት ላይ ብቻ ማድረጉ ለተጫዋቾቹ ትልቅ መረጋጋትን ይሰጣል።
አርሰናል በአሁኑ ወቅት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ያለውን ግፊት ለመቋቋም የአርቴታ ስብስብ የአዕምሮ ጥንካሬ እና ትኩረት ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው።
መድፈኞቹ የሰኞውን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ፣ ለተቀናቃኞቻቸው ማንቸስተር ሲቲ ብርቱ የቤት ስራ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዕጩዎች ይፋ ሆኑ
የአርሰናል የድል ጉዞ እና የዌስትሃም ቁጭት!
“በVAR ላይ እምነት የለኝም!” – ፔፕ ጋርዲዮላ