የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዕጩዎች ይፋ ሆኑ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዕጩዎች ይፋ ሆኑ

የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች አይን ያረፈበትና በከፍተኛ ፉክክር የታጀበው የ2025/26 የውድድር ዓመት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማጠናቀቂያው እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የሊጉን ኮከብ ተጫዋቾች ለመለየት የሚረዳው የዕጩዎች ዝርዝር ዛሬ ይፋ ሆኗል፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዓመት እጅግ አስደናቂ አቋም እያሳዩ የሚገኙት ሰሜን ለንደኖቹ አርሰናሎች፣ በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ ሦስት ቁልፍ ተጫዋቾችን በማካተት ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡

ዴቪድ ራያ፦ በግብ ጠባቂነት ዘርፍ ባሳየው ድንቅ ብቃትና ቡድኑን ከበስተጀርባ ሆኖ በመምራት ረገድ የነበረው ሚና ለዕጩነት አብቅቶታል፡፡

ጋብሬል ማጋሌሽ፦ በመከላከል ረገድ ያለው ጥንካሬና በቆሙ ኳሶች ላይ የሚያሳየው ግብ የማስቆጠር ክህሎት በአውሮፓ ግንባር ቀደም ተከላካይ እንዲባል አድርጎታል፡፡

ዴክላን ራይስ፦ የመሐል ሜዳው ሞተርና የቡድኑ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያሳለፈው ዓመት ለዚህ ትልቅ ክብር በዋና ተፎካካሪነት እንዲቀርብ ረድቶታል፡፡


የአምናው ሻምፒዮን ማንቼስተር ሲቲ በበኩሉ ሁለት ተጫዋቾችን ለዕጩነት አቅርቧል፡፡

የግቦቹ ማሽን ኤርሊንግ ብራውት ሀላንድ የተለመደ ጎል የማስቆጠር ብቃቱን በማስቀጠል ሲካተት፣ የቡድኑ አዲስ ፈርጥ አንቷን ሴሜኒዮ በሲቲ ቤት ባሳየው ፈጣን መላመድና ወሳኝ ተጽዕኖ በዝርዝሩ ውስጥ መካተት ችሏል፡፡

ከእነዚህም በተጨማሪ የማንቼስተር ዩናይትዱ ካፒቴን ብሩኖ ፈርናዴዝ ቡድኑን በመምራትና ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የነበረው ጽናት በእጩነት እንዲቀርብ አስችሎታል።

የብሬንትፎርዱ ብራዚላዊ አጥቂ ኢጎር ቲያጎ እናየኖቲንግሃም ፎረስቱ ሞርጋን ጊብስ ዋይት በግል ብቃታቸው ክለቦቻቸውን በመታደግ ያሳዩት ብቃት ለዕጩነት አብቅቷቸዋል፡፡


ይህ የዕጩዎች ዝርዝር እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ሽልማቱ በቡድን ስኬት እና በግል ብቃት መካከል የሚደረግ ፍልሚያ መሆኑን ነው፡፡

አርሰናል በሊጉ መሪነቱን እንደያዘ ሁሉ በዚህም ዘርፍ የበላይነቱን መውሰዱ የአሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ ስብስብ ምን ያህል የተሟላ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

በተለይም ዴክላን ራይስ እና ዴቪድ ራያ ከዝውውር በኋላ ያሳዩት ፈጣን ተፅዕኖ የዓመቱ ታላቅ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሆኖም እንደ ሀላንድ ያሉ የጎል አዳኞችና እንደ ብሩኖ ያሉ የጨዋታ አቀጣጣዮች መኖራቸው የሽልማት አሸናፊውን ለመተንበይ እጅግ አዳጋች ያደርገዋል፡፡

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዘጋጆች አሸናፊውን በቀጣዮቹ ሳምንታት በደመቀ ስነ-ስርዓት ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡



ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ