ሰርጂዮ ራሞስ ሲቪያን ለመግዛት ከስምምነት ደረሰ
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ እና የስፔን ብሄራዊ ቡድን የጀርባ አጥንት ሰርጂዮ ራሞስ፣ ወደ አሳደገው ክለብ ሲቪያ ለመመለስ የወሰደው እርምጃ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
የአንዳሉሲያዉን ክለብ ለመግዛት ለወራት ሲንከባለል የነበረው ድርድር በዛሬዉ ዕለት እልባት አግኝቷል።
የ40 ዓመቱ ራሞስ የሚመራው እና በ”ፋይቭ ኢለቨን” ፈንድ የሚደገፈው ጥምረት፣ ሲቪያን በ444 ሚሊዮን ዩሮ ለመግዛት በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሷል።
ከክለቡ ባለቤቶች ጋር የተደረገው ንግግር ከ8 እስከ 10 ሰዓታት የፈጀ ረጅም እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ የፋይናንስ ዋስትናዎች ቀርበው የባለቤትነት ሽግግሩን ለማጠናቀቅ ግንቦት መጨረሻ ወይም ሰኔ መጀመሪያ ቀጠሮ ተይዟል።
ሲቪያ በአሁኑ ወቅት በሜዳ ላይም ሆነ በቢሮ ውስጥ አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።
የክለቡ የተጣራ እዳ ወደ €90 ሚሊዮን ገደማ እንደሚጠጋ የሚገመት ሲሆን፣ ይህ መጠን ከጠቅላላው የሽያጭ ዋጋ ላይ የሚቀነስ ይሆናል።
በ2023-24 የውድድር ዘመን ብቻ ክለቡ የ€81.8 ሚሊዮን ኪሳራ አስተናግዷል።
በላ ሊጋው በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲቪያ፣ ካለው የመውረድ ስጋት የተነሳ ክለቡ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ቢወርድ ዋጋው ከ20 እስከ 30 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተሰግቷል።
ሰርጂዮ ራሞስ እግር ኳስን የጀመረበትን ክለብ ከመፍረስ ለማዳን የወሰደው ቁርጠኝነት አስገራሚ ሆኗል።
እ.ኤ.አ. በ2004 በሲቪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ በሪያል ማድሪድ እና ፒ.ኤስ.ጂ ደምቆ፣ በ2023 ወደ ቤቱ ተመልሶ ነበር። አሁን ግን ተጫዋች ብቻ ሳይሆን “ባለቤት እና አዳኝ” ሆኖ ሊመጣ ነው።
መጪዎቹ ሳምንታት ለሲቪያ ህልውና ወሳኝ ናቸው። ክለቡ በላ ሊጋው መቆየቱን ማረጋገጥ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የራሞስ ጥምረትም የቀረውን ክፍያ ፈጽሞ የባለቤትነት ማረጋገጫውን ለመረከብ በዝግጅት ላይ ነው።
ሲቪያ በአዲስ መልክ ሊወለድ ነው? ወይስ የራሞስ ትልቁ ቁማር? ጊዜው የሚመልሰው ቢሆንም፣ የእግር ኳስ አለም ግን አይኑን ደቡብ ስፔን ላይ ተክሏል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የአርሰናል የኋላ ደጀን ቤን ዋይት የውድድር ዓመቱ በጉዳት ተጠናቀቀ
ዣቪ አሎንሶ ለቼልሲው የአሰልጣኝነት ቦታ ዋነኛው እጩ ሆኖ ብቅ ብሏል
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ የሀገሪቱን ቋንቋዎች ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ ዘመኑን የሚመጥን የቋንቋ ልማት ማከናወን እንደሚገባ ገለፀ