በሊጉ የዋንጫ ፉክክር እና የህልውና ትግል

በሊጉ የዋንጫ ፉክክር እና የህልውና ትግል

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌና ጫፍ ላይ የሚገኙ ክለቦች እጣ ፈንታቸውን የሚወሰኑበት 36ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ አምስት ተጠባቂ ጨዋታዎች ይጀምራል።

ሳምንቱ በዋንጫ ፉክክሩ፣ በአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ እና ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ የታጀበ ነው።

የዕለቱ መክፈቻ ጨዋታ በታሪካዊው አንፊልድ ሮድ የሚደረግ ሲሆን፣ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚታትሩትን ሊቨርፑልንና ቼልሲን ያገናኛል።

ሊቨርፑል በዩናይትድ የደረሰበትን የሽንፈት ጠባሳ በመደምሰስ ወደ ድል መንገድ ለመመለስና በአራተኝነቱ ለመጽናት ይጫወታል።

በታሪኩ እጅግ አስከፊ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ሰማያዊው ክለብ፣ ባለፉት 6 ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።

ዛሬም የሚሸነፍ ከሆነ ከ74 ዓመታት በኋላ ለሰባተኛ ተከታታይ ጊዜ በመሸነፍ ጥቁር ታሪክ ይጽፋል።

ባለፉት 5 የእርስ በርስ ግንኙነቶች ሊቨርፑል 3 ጊዜ ሲያሸንፍ፣ ቼልሲ በ 2ቱ ድል ቀንቶታል።

ይህ ተጠባቂ ጨዋታ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በአንፊልድ ይካሄዳል።

የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎውን ያረጋገጠው ማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ስታዲየም ኦፍ ላይት አቅንቶ ከሰንደርላንድ ጋር ይጫወታል።

ዩናይትድ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ሲያልም፣ ሰንደርላንድ በበኩሉ ከሦስት ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ ለደጋፊዎቹ ድል ለመስጠት ይፋለማል።

ይህ ጨዋታ ደግሞ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ በስታዲየም ኦፍ ላይት ይደረጋል።

ባለፈው ሳምንት ነጥብ ጥሎ የአርሰናልን መንገድ ያመቻቸው ማንቼስተር ሲቲ፣ በኢትሃድ ስታዲየም ብሬንትፎርድን ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ያስተናግዳል።

ሲቲ ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ፣ ነገ አርሰናል ጨዋታውን እስከሚያደርግ ድረስ የነጥብ ልዩነቱን ወደ 2 ዝቅ በማድረግ በለንደኑ ክለብ ላይ የስነ-ልቦና ጫና መፍጠር ይችላል።

የሊጉ መሪ አርሰናል በነገው ዕለት ከሜዳው ውጭ ከዌስትሃም ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሳምንቱ ትልቁ ትኩረት ነው።

ሊጉን አርሰናል በ 76 ነጥብ ሲመራ፣ ማንቼስተር ሲቲ በ 71፣ ማንቼስተር ዩናይትድ በ 64 እንዲሁም ሊቨርፑል በ 58 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ