ጤናማ እና በስፖርት የዳበረ ዜጋ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ያለዉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድአሚን በደዊ ገለፁ

ጤናማ እና በስፖርት የዳበረ ዜጋ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ያለዉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድአሚን በደዊ ገለፁ

በልዩ ወረዳዉ የ8ኛ አመት የለውጥ ጉዞ እና የብልጽግና ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደርበት የምርጫ ምልክት የማስተዋወቅ እና የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መርህ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድአሚን በደዊ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባለፉት ስምንት የለዉጥ አመታት በሀገር ደረጃ ዉጤታማ ስራዎችን መሰራታቸውንና የቀቤና ልዩ ወረዳም የለዉጡ ቱሩፋት ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በአእምሮ የዳበረ፣ ጤናማ እና አምራች ዜጋ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ያለዉ ሚና ከፍተኛ ነዉ ያሉት ዋና አስተዳዳሪዉ፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ገልጸዋል።

ሰባተኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ሚና ጉልህ መሆኑንም አንስተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትልና የወልቂጤ ምርጫ ክልል የፓርቲዉ እጩ ተወዳዳሪ ወይዘሮ ዙልፋ አለዊ፤ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር ባለፉት አመታት ባከናወናቸዉ ተግባራት አበረታች ለዉጦች መመዝገባቸዉን ተናግረዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካፉ አረቦ በበኩላቸዉ፤ ፓርቲዉ ባለፉት አመታት በኢትዮጵያን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በዲፕሎማሲ መስኮችን ጨምሮ በሌሎችም የሚታዩ ለዉጦች ማምጣቱን አመላክተዋል።

እንደ ሀገር የተጀመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም የኢትዮጵያን ከፍታ በማረጋገጥ ተምሳሌት ሀገር ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልወሃብ ኑረዲን፤ ወጣቶች በስፖርቱ ዘርፍ እያሳዩት የሚገኘዉን ፍቅር፣ አንድነትና ንቁ ተሳትፎ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ማስቀጠል እንዳለባቸዉ ገልፀዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ አብሮነትን፣ አንድነትንና በየትኛዉም አካባቢያዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚያደርጋቸዉ የመርሃግብሩ ተሳታፊ ወጣቶች ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን