“ራያ በአርሰናል ቤት ድንቅነቱን እያስመሰከረ ነው” – ሚኬል አርቴታ
በለንደን ሰሜናዊ ክፍል፣ በኤምሬትስ ስታዲየም የሳር ሜዳ ላይ አንድ ስም በጉልህ እየተነሳ ነው። ስሙ ዳቪድ ራያ ይባላል። ወደ ክለቡ ሲቀላቀል ብዙዎች በጥርጣሬ አይን ቢመለከቱትም፣ ዛሬ ግን ያ ጥርጣሬ ወደ አድናቆት፣ ያ ስጋትም ወደ መተማመን ተቀይሯል።
የአርሰናሉ አለቃ ሚኬል አርቴታ ስለ ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ሲናገሩ አፋቸው አድናቆትን አይጠግብም።
አርቴታ እንደሚሉት፣ የራያ ብቃት “ከሚጠበቀው በላይ” እና “ልዩ” ሆኖ ተገኝቷል።
አርቴታ ስለ ስፔናዊው ግብ ጠባቂው በሰጡት አስተያየት “በመጀመሪያ ደረጃ፣ እሱ ልዩ ብቃት እያሳየ ነው። ክለቡን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ እያሳየ ያለው ወጥ የሆነ አቋም ምናልባትም ማንም ያልጠበቀው ነው”ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም “አንዳንድ ጊዜ እሱ የሚያደርጋቸውን አስገራሚ ነገሮች እንደ ተራ ነገር እንመለከታቸዋለን፤ ግን አይደሉም። በወሳኝ ሰዓታት ለቡድኑ የሚገባውን ምላሽ ሰጥቷል” ሲሉ ተናግረዋል።
የዳቪድ ራያ የዘንድሮ ብቃት በአንድ ቃል “አስተማማኝ” የሚባል ነው። አርቴታ “ልዩ” ሲሉት ዝም ብለው ሳይሆን በመረጃ የተደገፈ ነው።
ዳቪድ ራያ የ2025–26 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊግ የ”ወርቅ ጓንት ” ሽልማትን ቢያንስ በጋራ እንደሚያሸንፍ በይፋ አረጋግጧል።
በዘንድሮው የሊግ ጉዞ 17 ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር የወጣ ሲሆን፣ 3 ጨዋታዎች ብቻ እየቀሩት የቅርብ ተቀናቃኙ ጂያንሉጂ ዶናሩማ (13) ሊደርስበት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ራያ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 9 ጨዋታዎችን ያለ ጎል በማጠናቀቅ ፣ በአንድ የውድድር ዘመን ለአንድ የእንግሊዝ ክለብ ከፍተኛውን የ”ክሊንሺት” ሪከርድ የያዘውን የኤድዋርድ ሜንዲን (2020–21) ክብረወሰን ተጋርቷል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ያስመዘገባቸው 17 የሊግ ንፁህ የጎል መዝገቦች ፣ በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱ በአንድ የከፍተኛ ሊግ የውድድር ዘመን ያስመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው።
ራያ በቅርቡ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በተደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ላይ ጎል ሳይቆጠርበት በመውጣት፣ አርሴናል ለታሪካዊው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ እንዲያልፍ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
የራያ ስኬት ምስጢር ግን የግል ብቃቱ ብቻ አይደለም። አርቴታ ለዚህ ውጤት መላው ቡድኑን ያመሰግናሉ።
አርሴናል ለሶስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን በመከላከሉ ረገድ ያስመዘገበው ውጤት የሚደነቅ ነው። ይሁንና ራያ በመስመሩ ላይ የሚሰጠው መረጋጋት፣ የኳስ ቁጥጥር ችሎታው እና በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚወስዳቸው ውሳኔዎች ቡድኑን ወደ ሌላ ከፍታ አውጥተውታል።
ታሪክ አስደናቂ የሚሆነው በማይጠበቁ ሰዎች ድንቅ ስራ ሲሰራ ነው። ዳቪድ ራያ በአርሴናል ቤት እያደረገ ያለውም ይኸው ነው።
ተቺዎችን በዝምታ፣ ደጋፊዎችን በደስታ ያስመሰገነው ይህ ግብ ጠባቂ፣ የመድፈኞቹን የዋንጫ ህልም እውን ለማድረግ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የአርሰናል የድል ጉዞ እና የዌስትሃም ቁጭት!
“በVAR ላይ እምነት የለኝም!” – ፔፕ ጋርዲዮላ
ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ግብፅን ትገጥማለች