ሚኒስቴሩ በስምጥ ሸለቆ ሃይቆች እየተተገበረ በሚገኘው የ15 ዓመት እቅድ የኦዲት ሪፖርት ላይ በሃዋሳ ውይይት እያካሄደ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይኸው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ውጤታማነት ለማረጋገጥ “ብራይት ፕሮጀክት” በተባለ ፕሮጀክት የሚተገበረውን የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች የ15 ዓመት እቅድ የኦዲት ሪፖርት መገምገም ጀምሯል።
ውይይቱን ንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ፤ በሀገሪቱ በውሃ አስተዳደር ዙሪያ የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
በንግግራቸውም ኢትዮጵያ “የውሃ ማማ” ነች የሚለው የዘመናት ትርክት ትክክል አለመሆኑንና ሀገሪቱ በውሃ እጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ላለፉት አራት ዓመታት በትኩረት ሲሰራበት መቆየቱን ገልጸዋል።
እንደ ሃገር የተከለሰው የውሃ ፖሊሲ ውሃን እንደ ሀገር ደህንነት መነሻ ማድረጉንና በሃገሪቱ የሚገኙ 12ቱ ተፋሰሶች የየራሳቸው ባህሪና ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ይህንን ፍላጎት የሚያጣጥም የተፋሰስ እቅድ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱንም ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል በጋራ በተቀረጸው “ብራይት ፕሮጀክት” በሰባት ተፋሰሶች እንዲሁም በ”ባዘርኔት ፕሮጀክት” የደናክል ቤዚንን ጨምሮ በአጠቃላይ 86 በመቶ የሚሆኑ ተፋሰሶች በተቀናጀ እቅድ እየተመሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ወሳኝ የልማት ኮሪደር መሆኑን ያነሱት አቶ ደበበ፣ ተፋሰሱ ያለውን ውሃ በቀላሉ የሚያጣ በመሆኑ እቅዱን ውጤታማ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኦዲት ሪፖርቱም የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት መካተት የሚፈትሽ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት እቅዱን ለመከለስ ግብዓት የሚሰጥ መሆኑንም አክለዋል።
የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ወንድሙ ታዲዎስ በበኩላቸው፣ ተፋሰሱ ከ7 በላይ በሆኑ ሀይቆች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያነሱት።
የጽ/ቤቱ ዋና አላማ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መተግበር መሆኑን ጠቅሰው፤ በተፋሰሱ የ15 ዓመት እቅድ መሰረት ለአምስት ዓመታት ሲተገበሩ የቆዩ ተግባራት የኦዲት ሪፖርት በየንዑስ ተፋሰሱ ቀርበው ግብዓት እንደሚወሰድባቸው አመላክተዋል።
የብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ኮርድኔተር ዶ/ር ብዙነህ አስፋው በኩላቸው የጋራ ሀብትን በጋራ ማቀድ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተፋሰስ እቅድ ክልሎችን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ጠቅሰው፣ አተገባበሩ ሳይንስን፣ የመንግስትን ፍላጎትና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ዶ/ር ብዙነህ አክለውም የተፋሰስ እቅድ ምንነትን፣ አስፋላጊነቱን፣ አተገባበሩን እና ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ ያመጣውን ለውጥ ለተሳታፊዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
በምክክር መድረኩ ከሲዳማ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ኦሮምያ ክልሎች የተወከሉ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሴክተር አካላትን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚመለከታቸው ሀላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ በየንኡስ ተፋሰሱ በቀረቡ የኦዲት ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ውይይት የሚደረግ መሆኑ ታውቋል።
ዘጋቢ፡ ወንድወሰን ሽመልስ

More Stories
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደማገባ ተገለጸ
የታርጫ ህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ በርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
በ25 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የማሪ ቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል በርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ