7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደማገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደማገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እጩ ተወዳዳሪዎች ጥሪ አቀረቡ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የልማት ዕድገት ይበልጥ በማሳደግና ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እና የባህር በር እንዲመለስ ከግብ እስኪደርስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ(ኢሶዴፓ) ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ ዱናሞ ወዕመጎ እንደገለጹት በሀገራችን በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ የሚበረታታ በመሆኑ ያልተሰሩ የልማት ተግባራትን በማሟላት እና ለሁሉ ተደራሽ እና ፍትሀዊ እንዲሆን ፓርቲው የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተግባር የሚታዩ፣ የተሰሩ ስራዎችን አልተሰሩም እንዲሁም ያልተሰራውን ተሰርቷል ከማለት ተቆጥበን ያልተሟሉ የልማት ተግባራት እንዲሟሉ በማድረግ የሀገር ብልጽግና እንዲረጋገጥ ሁላችንም በጋራ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢሶዴፓ የባህር በር ይመለስ ጥያቄ ከ1983 ዓመተ ምህረት ጀምሮ እየጠየቀ የቆየ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዱናሞ በአሁኑ ወቅት መንግስት እየጠየቀ ያለው የባህር በር ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ፓርቲያቸው ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ አብሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ዕጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ተረፈ የኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ እና ሀገር ልማትና አንድነት ላይ አተኩራ እየሰራች ያለው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ያልተመለሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር የተጠናከረ የጋራ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ብለዋል።
የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ ተመስገን አበበ በበኩላቸው በሀገሪቱ ላይ ጠንካራ የልማት ተግባራት እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸው፥ ያልተሰሩ የልማት ስራዎች እንዲጠናከሩና ህብረተሰቡ የልማቱ ቀጥተኛና ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ፓርቲያቸው ተግቶ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
እንደሀገር እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ያልተሰሩ ልማቶች እንዲሰሩ፣ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ፣ ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ ኃይላት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ እና ምርጫው ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ተናግረዋል።
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከአካል ጉዳተኞች፣ ከሴቶች፣ ከአረጋውያን እና ወጣቶች ተወካዮቾ እንዲሳተፉ መደረጉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች አካችነትን ያረጋገጠ እና በቀጣይ በሀገሪቱ ሁሉን አሳታፊ የምርጫ ዕድል እንዲሰፋ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም የፓርቲ ተወካይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም በሰላማዊ መንገድ የፈለገውን ፓርቲ በመምረጥ የዜግነት ግዴታውን መወጣት አለበት ብለዋል።
በ21ኛ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተናግደው በሰለጠነ፣ በዲሞክራሲያዊ እና የሀሳብ የበላይነት በምርጫ አሸንፎ የሚመጣውን እንጂ በትጥቅ እና ጫካ ገብተው የሚዋጉትን አይደለም ሲሉም ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ እጩ ተወዳዳሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የታርጫ ህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ በርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
በ25 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የማሪ ቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል በርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ መዳን እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለጹ