የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ መዳን እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለጹ
ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል መሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ መዳን እንዳስቻላቸው በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ።
አባላት አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ሥራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እየተሠሩ መሆኑን የልዩ ወረዳው ጤና ጽ/ቤት አስታውቋል።
ካነጋገርናቸው የማህበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል በሙዱላ የመጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና ተሰርቶ ለረጅም ወራት ህክምናቸውን እየተከታተሉ ያሉት አቶ ሙሉቀን ወርቅነህ እና አስታማሚያቸው ወ/ሮ ደሳለች ታክሶ በሰጡን አስተያየት አባል መሆናቸው ካልተጠበቀ የገንዘብ ወጪ እንዳዳናቸው ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አባል በመሆናቸው አልፎ አልፎ የመድኃኒት እጥረት ሲያጋጥም ከውጭ ከመግዛት በስተቀር በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን ሁሉንም አገልግሎት በነፃ ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።
በሙዱላ የመጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታል የተኝቶ ህክምና ክፍል ባለሙያዎች ነርስ እርዳቸው ላመሮ እና አየለ ዓለሙ በሰጡት አስተያየት በክፍላቸው በተለያዩ ኬዞች ለሚታከሙ ታካሚዎች ሙያዊ እንክብካቤና ክትትል በማድረግ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሆስፒታሉ በርካታ አባላት በዓመት አንዴ በሚያወጡት መዋጮ ጠቅላላ አገልግሎቶችን በነፃ እያገኙ መሆኑን የጠቆሙት በሆስፒታሉ የማህበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ወልዴ በዶሬ ናቸው።
በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሙዱላ መጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ በየነ በበኩላቸው፥ የአጎራባች ወረዳዎችን ጨምሮ በሆስፒታሉ የሚገለገሉ ተገልጋዮች ብዛት ከፍተኛ በመሆኑ አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ የመድኃኒት እጥረት ባሻገር፥ ከፍተኛ ወጪ የሚያስውጡ የቀዶ ጥገና አገልግሎቶችን ጨምሮ የተለያዩ የውስጥ ደዌ ምርመራና ህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል።
መንግሥት በጤናው ዘርፍ ያመቻቸው ይህ የማህበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በርካቶችን ከሞትና ከአቅም በላይ ከሆነው ወጪ የታደገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በልዩ ወረዳው ጤና ጽ/ቤት የህክምና አገልግሎት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደስታ ድቃሶ በልዩ ወረዳው ባሉት በሦስቱም ጤና ጣቢያዎችና በሙዱላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና መድህን አገልግሎትን ጨምሮ ህብረተሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንድችል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ: ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በከምባታ ዞን ሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርአት (E-LMIS) ምዝገባ በይፋ መጀመሩን የከተማው ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት አስታወቀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ
ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ጨምሮ ለእሳት አደጋ መንስኤ የሚሆኑ የመጠቀሚያ ዕቃዎችን በጥንቃቄ በመጠቀም በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ