ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የኢሠራ ባሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሠረተ ድንጋይ አስቀምጧል

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የኢሠራ ባሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሠረተ ድንጋይ አስቀምጧል

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የኢሠራ ባሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ለበርካታ አመታት የኢሠራ ወረዳ እና ባሌ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የጤና መሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት በተሠራው ሥራ ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከዚህ ቀደም ለህክምና አገልግሎት የጊዜ እና የጉልበት መስዋዕትነት መከፈሉን አስታውሰው፥ ይኸው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ምላሽ የሚሰጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ቃልን በተግባር በማረጋገጥ ለህዝብ አገልግሎት የተሠጠውን ትኩረት ያሳያልም ብለዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት በታቀደው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የሚያስገነባው ይሄው ዘመናዊ ሆስፒታል 346 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየው የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመው፥ ወላድ እናቶች በቅርቡ አገልግሎት የሚያገኙበት በጤና ዘርፉ ያለው የተደራሽነት ጥያቄ ከመመለስ አኳያ ድርሻው የላቀ ነው ብለዋል።

የኢሠራ ባሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብነት በጋሻው መንግስት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን በማጠናከር የተሠሩ ተግባራት ያልተመለሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ የተገኘበት ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አዲስአለም ታዩ – ከዋካ ጣቢያችን