በ240 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጎፋ ዞን በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

በ240 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጎፋ ዞን በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ240 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጎፋ ዞን በቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የሆስፒታሉ መመረቅ ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረውን የጤና ተቋም ተደራሽነት እንደሚቀርፍ ተመላክቷል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፥ መንግስት እንደ ሐገር የህዝቡን የማህበራዊ ፍላጎት ለሟሟላት ዲጂታላይዝ የጤና አገልግሎት ከመሥጠት ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በክልሉም የተያዘውን የጤና አገልግሎት ግብ እውን ከማድረግ አኳያ የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፥ የበቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የዚሁ አንድ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

የበቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ሂደት ረዥም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግንባታውን ለማጠናቀቅ በመንግስት የተያዘውን አቋም ለደገፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ሆስፒታሉ ዛሬ ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆን የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፥ የዞኑ አስተዳዳሪና ካቢኔ አባላት እንዲሁም የወረዳው ነዋሪዎች ህዝቡን ከማስተባበር አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበራቸው አብራርተዋል።

የሆስፒታል አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው ብቁ የቦርድ አባላትን ማደራጀትና ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለዞኑ አስተዳዳሪ ከክልሉ መንግስት አንድ አምቡላንስ አበርክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ሆስፒታል ለግንባታው 170 ሚሊዮን ለቁሳቁስ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአከባቢው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን በማጠናከር የግልና የአካባቢን ጤና በመጠበቅ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን ተግዳሮት መሻገር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥቂት ያልተሟሉ ቀሪ የላቦራቶሪ ማሽኖች ባፋጣኝ የሚሟሉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ እንዳሻው፥ አሁን ባለው አቅም ከዛሬ ጀምሮ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሉ የተሟላ ቀዶ ጥገና ማድረግ የሚችል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የበቶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ጥያቄ በነዋሪው ዘንድ ረዥም ጊዚያትን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው፥ መንግስት ለጥያቄው በሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ የተሠማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በግንባታ ሂደቱ ላደረጉት ቀና ትብብርና በምረቃው ዕለትም ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አስተዳዳሪው፥ በቀጣይም የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በምረቃ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የበቶ ከተማ ከንቲባ አቶ አካሉ አምቦ፥ የበቶ ከተማ ከፍተኛ የቁም ከብትና የግብርና ሰብሎች ግብይት ማዕከል መሆኗን ጠቅሰው፥ ይህንን እምቅ አቅም ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ ጤናን መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን