ከ1 ሚሊየን 223 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የመሬት ልኬት ማድረግ እየተሰራ መሆኑን አሰታወቀ

ከ1 ሚሊየን 223 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የመሬት ልኬት ማድረግ እየተሰራ መሆኑን አሰታወቀ

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ቢሮው እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ 1 ሚሊየን 223 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የመሬት ልኬት በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሬት አስተዳደር አሰታወቀ።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሬት አስተዳደር በጂኦ ስፓሻል ዘርፍ በCAM-LA project በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬት ማስጀመሪያ ፕሮግራም አካሂዷል።

የገደብ ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪ ሲሳይ ታደሰ፥ መሬት የሀብት ምንጭ መሆኑን ጠቁመው፥ ልኬቱ መሬትን ማስተዳደርና መጠቀም ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት እንደሚረዳ አመልክተው፥ ለአርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነትን ከማረጋገጥ በዘለለ የታለያዩ ብድሮችን ለማግኘትና ሀብት ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል።

‎የጌዴኦ ዞን ዋና አሰተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር)፥ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ከሰጠው ሀብት መካከል መሬት አንዱ ቢሆንም፥ ከማስተዳደር አንፃር ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው፥ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የሚደረገው የመሬት ልኬት የፋይናንስ አገልግሎትን በማግኘት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

‎በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሬት አስተዳደ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ መሬት ከሀብቶች ሁሉ የከበረ በመሆኑ መንከባከብ እንደሚገባ ጠቁመው፥ ቢሮው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በቂ ዝግጅት በማድረግ 1 ሚሊየን 223 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮቻችን ልኬት ተደርጎላቸው፣ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር፣ በህጋዊ ሰነድ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎ልኬቱ በአፋጣኝ ተጠናቆ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

‎ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን