በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመማር ማስተማር ዘርፍ እየተመዘገቡ የሚገኙ ለወጦች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ
በዩኒቨርስቲው አሁን ላይ 11 ሺህ ያህል ተማሪዎች በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች በመደበኛና በተከታታይ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብቴ ዱላ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት ትርጉም ባለው መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዩኒቨርሲቲው በ8 ኮሌጆችና በአንድ ትምህርት ቤት በመጀመሪያ ዲግሪ በ51 የትምህርት ፕሮግራሞች፣ በድህረ ምረቃ በ2ኛ ዲግሪ በ40 ፕሮግራሞች እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ በ1 ፕሮግራም ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህም 11ሺህ ያህል ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የመምህራን አቅም ከመገንባት እና በሀገር ውስጥና ከሃገር ውጭ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የትምህርት ደረጃቸው ከማሻሻል እንዲሁም በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ከማሟላት እና ምቹ የመማሪያ አካባቢን ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
አክለውም ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን በመፍጠር ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየተሰጣቸው መሆኑን በመጥቀስ ይህን ተከትሎም በዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱንና የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ እንዲሁም የምሩቃን የመቀጠር ምጣኔ መጨመሩን አብራርተዋል።
የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ከመማር ማስተማር ጋር በማስተሳሰር ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እየተሰራ አንደሚገኝ በመጠቆም በቀጣይም በዩኒቨርስቲው በየደረጃው አየታየ ያለው ለውጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር እንደሚሰራ ነው ነው ያመላከቱት።
ስለሆነም በዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማሩ ተግባር በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አአስፈላጊውን ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፓርቲው መሪነት በልማት፣ በመልካም አስተዳደር እና በፖለቲካው ዘርፍ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል – አቶ ፍቅሬ አማን
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5.5 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ወደስራ መግባታቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ