ለሴቶች ሞት ምክንያት የሆነውን የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል እንደሚገባ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሐኪም ዶ/ር አረጋኸኝ ሙሉጌታ አሳሰቡ

ለሴቶች ሞት ምክንያት የሆነውን የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል እንደሚገባ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሐኪም ዶ/ር አረጋኸኝ ሙሉጌታ አሳሰቡ

ካንሰር ማለት ከማንኛውም የሰውነት ክፍል የሚነሳ እብጠት ሲሆን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚሠራጭ ሆኖ ለከፋ ህመም አለፍ ሲሊም ለሞት የሚዳርግ ነው።

በሆስፒታሉ የማህፀንና ፅንስ ክፍል የማህፀንና ፅንስ ሲኒየር ስፔሻሊስት ዶ/ር አረጋኸኝ ሙሉጌታ እንደገለፁት፤ የማህፀን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ተሠራጭቶ የሚገኝ ሲሆን የቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ መቆጣጠር ካልተቻለ ለከፋ የህመም ስቃይና ለሞት የሚዳርግ ነው።

የማህፀን በር ካንሰር መከላከል የሚቻል የካንሰር አይነት መሆኑን ዶ/ር አረጋኸኝ አስረድተዋል።

የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በትምህርት ቤቶች ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 14 የሆኑ ሴቶች የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳይጀምሩ በማስከተብና ‘በሂማን ፓፕሎማ ቫይረስ’ በሚከሰት ኢንፌክሽን በሽታው ስር ሰዶ ወደ ካንሰር እንዳይቀየር ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል።

ዶ/ር አረጋኸኝ ጨምረውም፤ አንዲት ሴት ልጅ ከ20 ዓመት በፊት የግብረ ስጋ ግንኙነት ከጀመረችና ከወለደች የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም፣ በኤች አይ ቪ የመጠቃትና ለማህፀን በር ካንሰር በብዙ እጥፍ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የደም መፍሰስ ዋንኛ ምልክቱ ስለሆነ ሴቶች በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መመርመር እንደሚገባቸው ዶ/ር አረጋኸኝ አስገንዝበዋል።

ሕይወት ውድ ስለሆነች ከፈጣሪ በታች እናት የልጆች ተስፋ በመሆኗ ሞታ ቤተሰብ እንዳይበተን ሁሉም እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች የማህፀን በርና የጡት ካንሰር ምርመራ በማድረግ ቅድመ ልየታ እንዲያደርጉ ዶ/ር አረጋኸኝ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ፀሐይ ጎበና – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን