7ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት “በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራ ምርምር ለዘላቂ ልማት፣ ጤና እና ሁሉን አቀፍ ደህንነት” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
በኮንፍረንሱ ላይ 29 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ነው የተመላከተው።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ ኮንፈረንሱ “በቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራ ምርምር ለዘላቂ ልማት፣ ጤና እና ሁሉን አቀፍ ደህንነት” በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ወቅቱን የሚመጥን መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ማህበረሰቡን እያጋጠሙ የሚገኙ ውስብስብ ችግሮችን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ስራዎችና ግኝቶቻቸው ዙሪያ ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው በማንሳት፤ ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ ጥያቄ በማንሳት፣ ምልከታቸውን በመሰንዘር እና ምሁራዊ ትስስራቸውን ይበልጥ በማጠናከር ረገድ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዮሀንስ ገብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
በኮንፈረንሱ ላይ 29 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው አስታውቀዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለ2 ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር አክመል መሐመድ (ዶ/ር)፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ሱልጣን ሱለይማን (ፕሮፌሰር) ቁልፍ ንግግር አቅራቢ፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፋሲካው አጣነው(ዶ/ር) ቁልፍ ንግግር አቅራቢ፣ ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ጥናት አቅራቢዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራን እንዲሁም ሌሎች እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
“አስቶን ቪላን ብወደውም ዩናይትድ ታላቅ ክለብ ነው” ዩሪ ቲሌማንስ
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የትምህርት ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም የተማሪዎች ቅበላ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው
የዳውሮ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ሥራ ዘመን 29ኛ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ