የቅድመ በሽታ መከላከል ተግባራትን በአግባቡ በመፈፀም ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወቅታዊ የቅድመ በሽታ መከላከል ተግባራትን በአግባቡ በመፈፀም ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ገለጸ፡፡
ከመጋቢት 18-21/2018 ዓ.ም ድረስ ቤት ለቤት የሚሰጠውን የ5ኛ ዙር የተቀናጀ ሀገር ዐቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ተካሂዷል።
በፖሊዮ ክትባቱ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ የተገኙት አቶ ለገሠ ጴጥሮስ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር፥ ይህ የፖሊዮ ዘመቻ ለ5ኛ ዙር እየተካሄደ ያለ መሆኑን ጠቁመው፥ ከዚህ ቀደም ስራው በተሳካ ሁኔታ እየተሰራ መቆየቱንና በዚህ ዓመት የዝግጅት ምዕራፉ በተቀናጀ ሁኔታ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀዋል።
እንደ ክልል ለ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ህፃናት ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የጠቆሙት አቶ ለገሠ፥ ከክትባቱ ባሻገር ቤት ለቤት በመዞር ያልተከተቡ ህፃናትንና ጀምረው ያቋረጡትን ተደራሽ ለማድረግ፥ ብሎም የምግብ እጥረት ያጋጠማቸውንና የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ህፃናት የመለየት ተግባራት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
ፖሊዮ በአሁን ሰዓት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በመጥፋት ደረጃ የሚገኝ በሽታ መሆኑን ጠቁመው፥ ህብረተሰቡ አንድ ህፃን ይህን የፖሊዮ ክትባት ባለመከተብ የሚከተለውን ተግዳሮት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ ሽጉጤ የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው፥ ሀገራችን ከዚህ ቀደም የምትከተለው የጤና ፖሊሲ መከላከልን መሠረት ያደረገ መሆኑን አመላክተው፥ በአሁን ጊዜ መከላከልና ማከምን በማጣመር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህ የፖሊዮ ዘመቻ መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልፀዋል።
ወቅታዊ የቅድመ በሽታ መከላከል ተግባራትን በአግባቡ በመፈፀም ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ባለድርሻ አካላትና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻውን ሊወጡ አመላክተዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የሸዋል ዒድ (ቀሊ ፍቼ) ባህላዊ ስርዓት በስልጤ
ሁሉም ሰው ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ በቀጣይ የሚያስተዳድረውን መንግስት መምረጥ እንዲችል የምርጫ ካርድ በወቅቱ መያዝ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ
በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ሁሉም ዜጋ የምርጫ ካርድ መያዝ እንደሚገባው ተገለጸ