የሸዋል ዒድ (ቀሊ ፍቼ) ባህላዊ ስርዓት በስልጤ
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ UNESCO በሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሸዋል ዒድ ከሀረሪ ክልል በተጨማሪ በዓሉ በደማቁ ከሚከበርባቸው የሀገራችን አከባቢዎች መከከል ስልጤ ዞን ተጠቃሸ ነው።
የስልጤ ህዝብ መጠሪያውን ያገኘው ከቀደምት የእስላማዊ ሱልጣኔቶች አመሰራረት ሲወርድ በመጣው ሂደት እንደሆነ ይነገራል። በተለይ ደግሞ ሀጂ አሊዬ ለልጃቸው ሱልጣን(ሱልጣኔት)፣ (ገዢ) የሚል ስም መስጠታቸውን ተከትሎ ስልጤ ለመጠሪያነት መዋሉን የተለያዩ ቦዞርፉ የተደረጉ የጥናት መረጃዎች ያመለክታሉ።
የስልጤ ማህበረሰብ በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ያሉት እንደመሆኑ ከኢድ አል ፈጥር በዓል ቀጥሎ ያሉ ስድስቱ የሸዋል ቀናት ከተጾሙ በኋላ የሚከበረው የሸዋል ስዒድ (ቀሊ ፍቼ) ትልቅ ትርጉም አለው።
በማህበረሰቡ ዘንድ በዋናው ኢድ አል ፈጥር እንዲሁም በትንሹ የሸዋል ዒድ የሚደረጉ ተግባራት ተለይተው ይታወቃሉ፤ የሸዋል ዒድ በስልጤ ማህበራዊ መስተጋብር ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን በበዓሉ የሚደረገው ዚያራ፣ ቤተዘመድ ጥየቃ፣ ወላጆች፣ በቤተዘመድ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ የተነፋፋቁትን በማገናኘት ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
ለዚህ ደግሞ የሴቶች ሚና ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ሴቶች ምግብ ለማዘጋጀት ለበዓል በማለት ቅቤን ጨምሮ ለአንዳንድ ወጭዎች ዕቁብ እስከመግባትም ይደርሳሉ። በሴቶች ገና ስማቸው ሲጠራ ጣዕማቸው ወደ አዕምሮ የሚመጣ ምግቦችን ለማዘጋጀት ምን ያህል አድካሚ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። እነዚህን ሁሉ ምግቦች ለማዘጋጀት በዓል ከመድረሱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ በሚደረጉ ዝግጅቶች መጀመርም የግድ ይላል።
ዒድን በስልጤ ልዩ የሚያደርገው በረመዳን ወር በአፍጥር ሰዓት ከደሃዎቹ ጋር አብሮ የሚበላ ሲሆን በሸዋል ኢድ ቀን ደግሞ በጥዋቱ ሰው ይዘያየራል፤ የተዘጋጀውን ምግብ ለብቻ አይበላም። እናቶችም ለበዓሉ በጣም ዝግጅት ያደርጋሉ፤ በስልጤ የጾም ፍቺ ሴቶች አይቤ ያዘጋጃሉ፤ የጎመን ክትፎ በቅቤ ይሠራሉ፤ በተለይም ለሸዋል ፍች ከአተር ክክ ከአይቤና በተለያዩ ቅመማ ቅመሞች የሚዘጋጀው ልዩ ምግብ ስሙ ጉጋ ይባላል፤ በጠዋት ለመብላት የሚዘጋጅ ሲሆን በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ ነው ።
ስልጤ ማህበረሰብ የሸዋል ኢድን ጨምሮ በበዓላትም ሆነ በዘወትር ቀናት በርካታ ባህላዊ ምግቦች የሚዘጋጅ ሲሆን አተካኖ፣ ሱልሶ፣ ሎሎሃድ፣ የበሰር ኪልፋን፣ ፊንታፊንቶ/ጨራጨረ፣ ጎሳ ጎሰ፣ የቆሊ /ያቆቀሲ በሰር..፣ የጄሪ አንገብሶ..፣ ዪንጫቆ በሰር የዶሮ ስጋ፣ የቁኜ ዪንጫቆ በሰር የመሳሰሉ የምግብ አይነቶችን በስፋት ማዘጋጀት የተለመደ ነው ።
የዒድ ዕለት ዚያራ ወይም ቤተዘመድ ጥየቃ ሲኬድ እንዲሁ በባዶ እጅ አይኬድም። ሁሉም የየአቅሙን ይዞ ይሄዳል። በተለይ በሸዋል ዒድ እና አረፋ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ያገኙበታል ፤ ለዚህም ነው ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሉ ፤ ባህሉን ጨምሮ የመጠያየቅ እና የመገናኘት በዓል በመሆን የሚያገለግል ሲሆን በትምህርት አልያም በሥራ ከዘመድ አዝማድ ርቀው የሚኖሩ ወጣት ስልጤዎች በዓልን ጠብቀው ወደቤተዘመድ መመለሳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። እርግጥ ነው ወደ ቤተዘመድ መምጫው በአረፋ ቢሆንም የኢድ አልፈጥር እና ሸዋል በዓላትም በርከት ያሉ ስልጤዎች ወደ ትውልድ መንደራቸው ይመጣሉ።
በስልጤዎች ዘንድ የሚታወቁ እና ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎባቸው የሚከበሩ በዓላት በርካቶች ናቸው። የእንዳች አረፋ(የሴቶች አረፋ)፣ አረፋ፣ ቀሊ ፍቼ(ትንሹ ኢድ)፣ መዉሊድ እና የስልጤ ዘመን መለወጫ (መሰሮ) ተጠቃሾች ናቸው።
ዘጋቢ: ሙጂብ ጁሀር – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የቅድመ በሽታ መከላከል ተግባራትን በአግባቡ በመፈፀም ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
ሁሉም ሰው ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ በቀጣይ የሚያስተዳድረውን መንግስት መምረጥ እንዲችል የምርጫ ካርድ በወቅቱ መያዝ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ
በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ሁሉም ዜጋ የምርጫ ካርድ መያዝ እንደሚገባው ተገለጸ