የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር በከተማው እየታዬ ያለውን እድገት ማስቀጠል እንደሚገባ በደቡብ ኦሞ ዞን የዲመካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
አንኳር የሆኑ የልማት አውታሮችን ከማስፋፋት በተጓዳኝ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።
አርብቶ አደሮቹ የሐመር፣ ካራና ኤርቦሬ በአብሮነት በሚኖሩባት የሐመር ወረዳ ለረጅም ዓመታት በመዲናነት ስታገለግል የቆየችው የዲመካ ከተማ በቅጡ የመሰረተ ልማት ተቋማት ሳይሟሉላት ቆይታለች።
በቅርቡ በአዲስ መልክ ለተዋቀረው ዞን በመቀመጫነት መመረጧን ተከትሎ ከተማዋ አዳዲስ የልማት አውታሮች እየተገነቡላት ሲሆን፥ የእነዚህ ተቋማት መስፋፋት ከተማዋን እያነቃቃት መምጣቱን ነው ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ አይናለም በለጠና ወ/ሮ የሺእመቤት ታመነ የሚገልጹት።
ለከተማ እድገት ወሳኝ የሆነው የአስፋልት ስራ መጀመርም የከተማዋን መጻኢ ተስፋ ብሩህ ማድረጉን ጠቅሰው፥ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በፍጥነት መሟላት አለባቸው ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
እንደ ዞኑ መቀመጫ የምትመጥን የከተማነት ደረጃን ታሟላ ዘንድ መንግስት ጅምሩን ያጠናክር እኛም የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ም/ከንቲባ አቶ ዮሐንስ ገርሾ በከተማ አስተዳደሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን የማስተፋፋቱ ስራ በተለያዩ መስኮች እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የቢሮ ግንባታን ጨምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃና የመብራት አገልግሎቶችን ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይገኙበታል ብለዋል።
የገብይት ቦታዎችን ምቹ የማድረግ ስራም እንዲሁ።
በቅርቡ መቀመጫ ከሆነች ወዲህ በከተማ አስተዳደር መዋቅር መመራት የጀመረች ሲሆን ለዚሁ የሚያስፈልጉ የልማት አውታሮችን ለማሟላት ጥረቶች በመጀመራቸው ለውጦች እየታዩ መጥተዋል የሚሉት ደግሞ ከንቲባው አቶ ወሌ አልማ ናቸው።
የኢንቨስመንት ልማትን በማፋጠን ከተማዋን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ከንቲባው ወደ ከተማዋ ለሚመጡ አዳዲስ አልሚዎች በራቸው ክፍት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በአከባቢዉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
የአከባቢን እና የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻለው ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ ሲቻል መሆኑ ተገለጸ
ምክር ቤቱ በጋሞ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ3 ሚላዮን ብር ድጋፍ አደረገ