በአከባቢዉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፡ መጋቢት 17/2018 (ደሬቴድ) በአከባቢዉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዜር እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በአሪ ዞን የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ ።
የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ካሳሁን ጌታቸዉ እንደገለፁት ኮሌጁ እያከናወነ ከሚገኘው የመማር ማስተማሩ ስራዉ ጎን ለጎን የበቆሎ፣ የማሽላ እና የአደንጓሬ ምርጥ ዜሮችን ለማባዛት ወደ 12 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ ዘር የመዝራት ስራ መጀመሩን ነዉ የገለፁት ።
ምረጥ ዘር የማባዛቱ ስራ እየተከናወነ የሚገኘው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጥ ዘር ኤጄንሲ፣ ከጂንካ ማረሚያ ተቋም እና ከአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ጋር በጋራ ትብብር መሆኑን ዲኑ ተናግረዋል፡፡
አክለውም ከ30 እስከ 40 ኩንታል ዘር ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።
በጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአዝርዕት ልማት ትምህርት ክፍል ኃላፊው መምህር ፍፁም ድንቁ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የምርጥ ዘር ብዜት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል። ይህም ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን በመስክ ልምምድ እንዲያዳብሩና ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የአሪ ዞን ግብርና መምርያ ኃላፊ ተወካይና የቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጋናእክሽ አርዳኪ እንደገለጹት ኮሌጁ ያስጀመረው የምርጥ ዘር ብዜት ለውጤት እንዲበቃ መምሪያው የሚጠበቅበትን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል፡፡
ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የአረም ክትትልና የተባይ መከላከል ስራዎችን እንዲሁም የሚመረተው ምርጥ ዘር በላብራቶሪ ተመርምሮ እስኪያልፍ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አቶ ጋናእክሽ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ተግባሩ የዞኑን አርሶ አደር የዘር አቅርቦት እጥረትና ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡
ኮሌጁ የሚያመርተው ምርጥ ዘር ከዞኑ አልፎ ለሌሎች ክልሎች የሚተርፍ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ጅማሮ መሆኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡_ዳኛቸው ደሴ – ከጂንካ ቅርንጫፍ ጣቢያችን

More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ እና የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዕቅድ ዙሪያ በታርጫ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው
ኦሞ ባንክ ሳውላ ዲስትሪክት በ2018 በጀት ዓመት ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ቁጠባ ማስመዝገቡን ገለጸ
እየተካሔደ ያለው ሀገራዊ ምክክር በሀገሪቱ አንድነት እና ሠላም ለማስፈን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ