ሀዋሳ፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአከባቢና የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻለው ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ ሲቻል መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌያት በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ማዕከላት አገልግሎት ስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ እንደተናገሩት፥ የዘመኑን ዕድገትና ስልጣኔ ተከትሎ ወንጀሎች እየተስፋፋ መምጣቱን አመላክተው፥ በክልሉ የጸጥታ ምክር ቤትም በዕቅድ እየሰራ ካለው ተግባር መካከል አንዱ እና ዋነኛው ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ ነው ብለዋል።
በሀድያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ የተገነቡ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ማዕከላትም ማህበሰቡን የሰላም ባለቤት ከማድረጋቸውም ባሻገር አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ አጋዥ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፥ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በዞኑ ለሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ሲሆን፥ ለዚህም የፖሊስ ማዕከላትን እስከ ታችኛው መዋቅር ማስፋፋት ላይ ትኩረት መደረጉን አመላክተዋል።
በጎምቦራ ወረዳ የተገነቡ የፖሊስ ማዕከላትም ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ማእከላቱ ህዝቡ አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኝ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት አቶ ማቴዎስ፥ ሌሎች ወረዳዎችም ልምድ እየወሰዱ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የሃዲያ ዞን ፖሊስ አዛዥ ም/ኮማንደር ተሾመ ባቲሶ በበኩላቸው፥ ማዕከላቱ ለማህበረሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት በአንድ ማዕከል መስጠትን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
አንድ ማእከል ከሶስት እስከ አምስት የሚደርሱ ቀበሌያትን የሚያቅፉ መሆናቸውን ያነሱት ም/ከማንደር ተሾመ፥ ወንጀልን በመከላከሉ ሂደት ህዝቡ ከፖሊስ ጋር በጋራ የሚሰራበት ማዕከል ስለመሆኑም አንስተዋል።
በቀጣይም በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች ተመሳሳይ ስራ እንደሚሰራ በመጠቆም።
ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ጎበና እንደገለጹት፥ በማህበረሰብ ተሳትፎ ወንጀልን በመከላከል አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር የተገነቡት ተቋማት ወሳኝ ናቸው።
ያነጋገርናቸው አንዳንድ የወረዳው ነዋሪዎችም ከዚህ ቀደም የፖሊስ አገልግሎትን ለማግኘት እስከ ወረዳ ይጓዙ እንደነበረና ይህም ለተለያየ እንግልትና ወጪ ይዳርጋቸው እንደነበር አስተውሰው፥ አሁን ግን በአካባቢያቸው ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ማዕከላት መከፈታቸው አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኙ ዕድል የፈጠረላቸው ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በዕለቱም የወረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እና የፖሊስ ጽ/ቤት ህንፃ ግንባታ መሠረት ድንጋይ የማኖር ስነስርዓት ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳን ጨምሮ የክልል የዞን እና የጎምቦራ ወረዳ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣የፖሊስ አባላት እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ምክር ቤቱ በጋሞ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ3 ሚላዮን ብር ድጋፍ አደረገ
የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ የበና ጸማይ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
በክልሉ ከቱሪዝሙ ዘርፍ ባለፉት 9 ወራት 925.6 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል