በኮንሶ ማህበረሰብ ዘንድ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት “ኼልታ” ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ እንደሚሰራ ተገለጸ

በኮንሶ ማህበረሰብ ዘንድ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት “ኼልታ” ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ እንደሚሰራ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮንሶ ማህበረሰብ ዘንድ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት “ኼልታ” ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለቀጣይ ትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የኮንሶ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በየ18 ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚተከለውና የሰላም እንዲሁም የኃላፊነት መሸከም አርማ የሆነው የ”ኦላህታ” ተከላና የሥልጣን ሽግግር ሥነ-ሥርዓት በኩይሌ ማህበረሰብ ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአካባቢው የባህል አባት አቶ ሮቦ ለሚታ እንደገለጹት፤ ይህ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ዘመናዊ መዋቅር ከመዘርጋቱ በፊት ሕዝቡ ራሱን ሲያስተዳድርበት የቆየ መሆኑን አስረድተዋል።

በኩይሌ የሥልጣን ሽግግር ሂደት ውስጥ “ህርፓ” እና “ካልኩሳ” የተሰኙ ሁለት ኼልታዎች (ባህላዊ ፓርቲዎች) መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ሮቦ፤ የሥልጣን ርክክቡም በእነዚህ ወገኖች መካከል በየ18 ዓመቱ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

አክለውም መንግሥት ለባህል ልዩ ትኩረት በመስጠቱ፣ ሁሉም አካል እነዚህን እሴቶች ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ የማሸጋገርና የማስተዋወቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ መክረዋል።

የሥልጣን ተረካቢው ትውልድ አባል ወጣት አማኑኤል ገመዳ በበኩሉ፣ አባቶች ያቆዩትን ይህን ዕሴት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል።

የካራት ከተማ አስተዳደር ባህልና ስፖርት ዩኒት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ካራፎ እና በዩኒቱ የባህል፣ ታሪክና ቅርስ ጥናት ባለሙያ አቶ ጉማቸው ሮብቶ ደግሞ ኩነቱ በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ መንደሮች ሁሉን አቀፍና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን ተናግረው፤ በሌሎች አምባ መንደራት እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

የኮንሶ ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃ ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ ደመላሽ አያኖ እንደገለጹት፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን ከመጠበቅ ባሻገር፣ ሌሎች ያልተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ ጥናት እየተደረገ ይገኛል።

የዞኑ ባህልና ስፖርት መምሪያ የቡድን መሪ አቶ ፈይሳ ለሚታ በበኩላቸው፣ የኮንሶን ሕዝብ ባህልና እሴት ለትውልድ ለማሸጋገር ጥናትና ምርምር በማድረግና ባህላዊ ፌስቲቫሎችን በመደገፍ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ የሥልጣን ሽግግር ሥነ-ሥርዓት የባህል አባቶች፣ ከአጎራባች አካባቢዎች የመጡ እንግዶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና መላው ማህበረሰብ በተገኘበት በሰላም ተጠናቋል።

ዘጋቢ: አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን