የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ህልውናን ለማስጠበቅ ይሰራል – የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ

የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ህልውናን ለማስጠበቅ ይሰራል – የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ

‎ሀዋሳ፡ ታኅሣሥ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ህልውናን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ፡፡

‎”የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ቃል የሠላምና የአንድነት ኮንፈረንስ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

‎ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ለማ ፖሎ፣ ባሻ ሮቦ ኩሴ፣ በቀለ ሞጎስ፤ መንግስት የህብረተሰቡን ችግር ሰምቶ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረቶች የሚበረታቱ መሆኑን ጠቁመው ከሰላም፣ ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ደህንነት፣ በመንገድ መሰረተ ልማትና በአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች በትኩረት ሊፈታ ይገባል ብለዋል።

‎ኢትዮጵያ ወደላቀ ደረጃ እየተሸጋገረች ትገኛለች ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ ብልፅግናዋን እንድታረጋግጥ የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ባዳዎች በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተው በተለይም ውጭ ሀገር ተቀምጠው የኢትዮጵያን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት ላይ መንግስት ጠንካራ አቋም ሊይዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎የጉባ ትርፋቶችን በተስፋ እየጠበቅን እንገኛለን ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ በአገሪቱ የተከናወኑ የልማትና የዲሞክራሲ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ስራዎች አመርቂ እመርታ እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል።

‎ከተሳታፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ፤ መንግስት በየደረጃው የሚነሱ ጥያቄዎችን በትኩረት እንደሚፈታ አረጋግጠው ችግሮችን ለመፍታት የማህበረሰቡንም ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አንስተዋል፡፡

‎ያሉንን ሀብቶች በአግባቡ ከተጠቀምንና ተናበን ከሰራን በአጭር ጊዜ ለውጥ እናመጣለም ሲሉ አረጋግጠዋል አቶ ገብረመስቀል።

‎የኢትዮጵያ መረጃ ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቴዘር ገ/እግዚአብሔር፤ በአርባምንጭ ከተማ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ ባለፈ ሁሉን አቀፍ ርብርብ በሚጠይቁ የልማትና የለውጥ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት መስራት ያሻል ብለዋል።

‎ሰላምን ለማስፈን ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የጠየቁት አቶ ቴዘር፣ የማምረት አቅምን ከማሳደግ ባለፈ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

‎የጋሞ ዞን በሰላምና ጥበብ ይታወቃሉ ያሉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ሰላምና ጥበብ ወደ ልማት እና ብልፅግና እያሸጋገረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

‎ከሰላም ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ህልውና ለማስጠበቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

‎የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን መፍታት ያሻል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህገወጥነትን በመከላከል የቁጠባ ባህላችንን ማሳደግ አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

‎ፀጋዎችን ከመጠቀም፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የትምህርት ጥራትንና ተጀራሽነት ለማሻሻል መንግስት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማሸነፍ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የብልፅግና ፓርቲ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ምላሽ የተሰጣቸውን ተግባራትን በማድነቅ ጊዜ የሚፈልጉትን ችግሮች ለመፍታት እንሰራለን ብለው ለዚህም ከሁላችንም ብዙ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን