የሴቶችና ህፃናት ጥቃት ለመከላከል ቅድሚያ ከራስ መጀመር እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ ገለፁ

የሴቶችና ህፃናት ጥቃት ለመከላከል ቅድሚያ ከራስ መጀመር እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ ገለፁ

ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለፁት በክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ አዘጋጅነት “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት /የነጭ ሪቫን ቀን/ ክልላዊ ማጠቃለያ በወልቂጤ ከተማ በተካሔደበት ወቅት ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ የሴቶችና ህፃናትን ጥቃት ለመከላከል ቅድሚያ ከራስ መጀመር እንደሚገባ ተናግርዋል።

ጥቃቱን ለመከላከል በተለያዩ ጊዜያት የግንዛቤ ትምህርት እየተሠጠ ቢሆንም መሠረታዊ የባህሪ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱ በጊዜ ያልተሰጠ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል የሚል አሠራርን በመከተል የሴቶችና ህፃናትን ጉዳይ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አመላከተዋል።

የአፈፃፀም ክፍተት የሚፈጥሩ ዳኞች እንኳን ቢኖሩ ከተጠያቂነት እንደማይድኑ ነው የገለፁት።

ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ለፍርድ ቤቶች አጋዥ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በህግና በባህላዊ ሽምግልና የሚፈቱ ጉዳዮችን መለየት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ የሚረዳ የህግ ማዕቀፍ በዝግጅት ላይ አንደሆነም አመላክተዋል።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድ ናስር እንዳሉት የነጭ ሪቫን ቀን መከበር የተጀመረው በወንዶች ሲሆን መብታቸውን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ ባሉ 14 ሴት ልጆች ላይ በአንድ ወጣት በተፈፀመ የግድያ ወንጀል መነሻነት መሆኑን አመላክተዋል።

የዘንድሮ አለም አቀፍ የፀረ ፆታ ጥቃት ቀን “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 16 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን በየደረጃው ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ሲከበር መቆየቱን ወ/ሮ ዘቢባ አንስተዋል።

ፆታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድረጊቶች በአብዛኛው የሚፈፀሙት በሴቶችና ህፃናት ላይ መሆኑን ጠቅሰው የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በተከበረበት ማግስት የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን ማክበራችን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በሴቶችና ህፃናት ላይ ፆታን መሠረት ያደረገ ማንኛውም አይነት ጥቃት የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን በመጠቆም ይህም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

ይህንን መሠረት በማድረግ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥቃቱን ላለመፈፀም በሌሎች ሲፈፀምም አይቶ ላለማለፍ ወንዶች በደረታችን ላይ የምናደርገው ነጭ ሪቫን በተግባር ልንተረጉመው ይገባል ሲሉም አክለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ሽመልስና መልአከሠላም ካሱ መኮንን በሰጡት አስተያየት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ስለሚያስከትሉ በየደረጃው ያሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከርና ግንዛቤ በመፍጠር ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ፆታዊ ጥቃት በህግ ወንጀልና በሃይማኖትም ሃጢያት በመሆኑ በሥነ ምግባር ዙሪያ የምንሰራቸው ስራዎች በትኩረት ልንቃኛቸው ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ: እቴነሽ ቲሬቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን