በተለያዩ የልማት መስኮች ሴቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ
ሀዋሳ፡ ታሕሣሥ 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በካፋ ዞን የሳይለም ወረዳ ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት በተለያዩ የልማት መስኮች ሴቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በወረዳው የያዶታ ከተማ እና የማሻሚ ቀበሌ ሴቶችበሰጡት አስተያየት በግብርና ልማት ዘርፍ ላይ በመሳተፋቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱቱ ገልጸዋል፡፡
በወረዳው 447 የልማት ህብረት በማደራጀትና በአንድ ለአምስት በማቀናጀት ወደሥራ ማስገባት መቻሉን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ቦጋለ ተናግረው፥ ሴቶችን በገጠርና በከተማ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሳታፊ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው በብለዋል።
ማደራጀት ብቻውን ግብ አይሆንም ያሉት ኃላፊዋ፥ በሂደቱ አንዳቸው ከአንዳቸው ልምድ እየተለዋወጡ ከሚያገኙት ገቢ መቆጠብ እንዲችሉ መደረጉን ጠቁመው፥ ያገኙትን ተሞክሮ በየጓሯቸው በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተጠቃሚ ሴቶች መካከል የመሻሚ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አልማዝ ልጋባ እና ወ/ሮ አልማዝ ወዳጆ ከተደራጁ አጭር ጊዜ ቢሆንም ድንች አምርተው መጠቀማቸውን አስታውሰው፥ ማህበራቸው 47 አባላትን ይዞ በ2 ሄክታር ማሳ ላይ በሙሉ ፓኬጅ ስንዴ ማምረታቸውን ገልጸው በቀጣይ በንብ እርባታና በበሬ ድለባ ዘርፍ ለመሰማራት ከወዲሁ ቁጠባ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በያዶታ ከተማ የኢባረዮ ማህበር አባል የሆኑት ወ/ሮ አረጋሽ ሁሴንና ወ/ሮ አለሚቱ ደምሴ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ምንም የገቢ ምንጭ እንዳልነበራቸው ጠቅሰው ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ውጤት አግኝተናል ይላሉ።
ባለፈው ዓመት ማሳቸውን በክራይ በማሳረስ ካመረቱት ድንች ሺያጭ 42 ሺህ ብር አግኝተው የእርሻ በሬ መግዛታቸውንና ከ85 ሺህ ብር በላይ መቆጠብ መቻላቸውን ገልጸው፥ የሥራ ተነሳሽነትንና መነቃቃትን እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
በዘንድሮ የመኸር እርሻ ሁለት ሄክታር ጤፍ እያለሙ ሲሆን በቀጣይ በጓሮ አትክልትና በእርባታ ዘርፍ ለመሥራት መዘጋጀታቸው ተናግረው፥ ከማጀት ወደ ማሳ የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማስፋት ተጠቃሚነታቸውን በላቀ ቁርጠኝነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት እና ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት በወልቂጤ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሔደ ነው
ከመማር ማስተማር ተግባር ባለፈ የአካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሚዛን ግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) መጭው ጊዜ ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን የምንሸጋገርበት ብሩህ ዘመን መሆኑን ተናገሩ