“ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል” – ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ

“ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል” – ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ

በአለምሸት ግርማ

የገቢ ግብር ሰብስቦ ለታለመለት ዓላማ ማዋል የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም፥ ግብርን በወቅቱ በታማኝነት መክፈል የዜጎች አገርን የመውደድና የዜግነት ኃላፊነትን የመወጣት መገለጫ ነው። በመሆኑም መንግስት ህግና ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት በየወቅቱ ግብርን ይሰበስባል።

የግብር ዋነኛ ዓላማ የመንግሥትን ገቢ ከፍ በማድረግ የዜጎችን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የአገርን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማፋጠን ነው። እንደ ሀገር በየዓመቱ በዕቅድ የተደገፈ ገቢ ከግብር ይሰበሰባል።

በዚሁ መሰረት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ለ2018 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደው እቅድና በሩብ ዓመቱ የተሰበሰበው የገቢ መጠን፣ እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ እንደሚከተለው አቅርበናል፦

አቶ ተስፋዬ አሰፋ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገቢ ጥናት የታክስ ትምህርት ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። የተቋሙን የሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተውናል፥

“የገቢ ስራው በተሳለጠ መንገድ እንዲከናወን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ 2018 በጀት ዓመት መሸጋገር ተችሏል። በዋናነት ትኩረት ከተደረገባቸው ስራዎች መካከል ሀብት መሰብሰብ፣ የወጪ ፍላጎትን ዳር ማድረስ፣ የዕቅድ ተግባቦት መድረኮች ማካሔድ፣ ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ አቅም መፍጠር፣ የአሠራር እና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ልህቀት፣ የህግ ተገዢነት አመራር ልህቀትና ዘላቂ የገቢ ዕድገት ለማስገኘት የግንዛቤ መፍጠሪያ የንቅናቄ መድረኮችም ተካሒደዋል።

“የንቅናቄ መድረኩ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ ሲሆን፣ ከ91 ሺህ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች 20 ሺህ የሚሆኑት በቴሌብር እንዲከፍሉ በማድረግ ከቤታቸው ሆነው ጊዜያቸውን ሳያባክኑ መክፈል የቻሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል። የገቢ ስራ የሁሉም አጀንዳ እንዲሆን በክልል ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጧል። ውጤቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።

“በባለፈው በጀት ዓመት 20.3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 16 ቢሊየን 9 መቶ ሚሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል። በየዓመቱ መሻሻል በመታየቱ በ2018 ደግሞ ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋቱ በዚህ ዓመትም ዕድገት ታይቶበታል።

“የታክስ ህግ ማስከበር በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው ‘ደረሰኝ የመስጠት ግዴታን’ በተመለከተ ሲሆን፣ በየሳምንቱ ቨርቹዋል ግምገማ በማካሔድ ስራዎች የሚመዘኑበት አሰራር እየተተገበረ ይገኛል። በህግ ማስከበር ዝርዝር የትግበራ ማዕቀፍ ገቢን ሊያሰፉ የሚችሉ ተግባራት ተከናውነዋል። እንዲሁም ቀድሞ የነበሩ የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ እንዲደረግ ተሰርቷል፤ ከዚህም በተጨማሪ የግንዛቤና ህግ ማስከበር ስራው በትኩረት እየተሰራ ነው።”

እስካሁን በተሰራው ስራ አዳጊ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን፤ በክልሉ የሚገኙ ሰባት ሺህ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል።

የታቀደውን ዕቅድ በተገቢው ለማሳካት ለ200 የዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና እንደተሰጠ እና በዞንና በልዩ ወረዳ ላሉ ግብር ከፋዮች ደግሞ የገፅ ለገፅ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በ2018 በጀት ዓመት 23 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ የካቲት ወር ድረስ 80 በመቶ እና መቶ በመቶ ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራበት እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ ጠቅላላ ገቢ 5 ቢሊየን 903 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፤ በክንውኑ 3 ቢሊየን 562 ሚሊየን ለመሰብሰብ ተችሏል። ክንውኑ ዕቅዳችንን እንድንከልስ አስችሎናል በማለት ያብራራሉ።

እንደ ቢሮው ምክትል ኃላፊ ገለጻ፣ በተቋሙ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻልን በተመለከተ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ራሱን የቻለ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በተቋም አመራርና ሠራተኞች ውይይት ተደርጎበት በዝርዝር እንደ ተቋም 16 ውስጣዊ እና 4 ውጫዊ ችግሮች ተለይተው በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 4 ችግሮችን ለመፍታት ታቅዶ 3 (75 በመቶውን) መፍታት መቻሉን የሩብ ዓመቱ አፈፃፀም ያሳያል።

ዕቅዱን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ በቂ የሰው ሃይል መኖር ወሳኝ በመሆኑ፥ ይህንን በተመለከተ በዓመቱ መጨረሻ የሰው ኃይሉን ወደ 2 ሺህ 950 ለማድረስ የተያዘውን ግብ እንዲሳካ እና በየአስተዳደር እርከኑ ያለውን የሰው ሀይል እጥረት ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በልዩ ትኩረት መስራት የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በዚህ ሩብ ዓመት 16 አዲስ የሰው ሀይል በየመዋቅሩ እንዲሟላ በማድረግ በ2017 ማጠቃለያ 66.60 በመቶ የነበረውን የሰው ሀይል አፈጻጸም አሁን ላይ 67.05 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

የገቢ ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሥራዎችን በተመለከተ አፈፃፀሙ እንደሚያሳየው፥ የተዘጋጀውን ዓመታዊ የገቢ ፊዚካልና ፋይናንሻል ሥራዎች ዕቅድ መነሻ በማድረግ ክልል ማዕከልን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች በየዳይሬክቶሬቱ የ15 ቀናት ዕቅድ ከተዘጋጀ በኋላ አፈጻጸሙ ለዘርፍና ለተቋሙ እንዲቀርብ በማድረግ ሪፖርቱ በዝርዝር እየተገመገመ በአፈጻጸም ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ግብረ-መልስ እየተሰጠ መሠራት እንዳለበት በቢሮዉ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።

አክለውም በመሆኑም በክልል ማዕከል ለሁሉም ዘርፎችና ዳይሬክቶሬቶች የሀምሌ እና ነሀሴ ወር በቼክሊስት የተደገፈ ድጋፍና ክትትል ተደርጎ የጽሁፍ ግብረ-መልስ በጥንካሬና በድክመት ተለይቶ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

 የክልል ማዕከል ዘርፎች እና ዳይሬክቶሬቶች ከአስሩም መዋቅር አስተባባሪዎች ጋር የ2018 በጀት ዓመት ውል ስምምነት ተዘጋጅቶ መፈራረም መቻሉንም ምክትል የቢሮ ኃላፊው የሰጡን መረጃ ያመለክታል፡፡

የ2018 በጀት ዓመት የ29 የከተሞች የመደበኛ እና የማዘጋጃ ቤት የሁለት ወር የገቢ አፈጻጸም በዞን እና በልዩ ወረዳ ደረጃ ተደራጅቶ ለከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና ለክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ተደራሽ መሆኑን ጠቅሰው የ2017 የሶሾ ኢኮኖሚ የገቢ መረጃ በመዋቅር በገቢ አይነት በዝርዝር በተጠየቀው ቅጽ መሠረት ለፕላንና ልማት ቢሮ እንዲደርስ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ማብራሪያቸውን ይቀጥላሉ፡-

“የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ተደራሽነትና አጠቃቀምን በተመለከተም በግብር ከፋዩ እጅ ያሉ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች በተገቢው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በቂ ቁጥጥርና ክትትል ከማድረግ ጎን ለጎን ከአቅራቢዎች ጋር በቅንጅት በመስራት በሩብ ዓመቱ 137 ግብር ከፋዮች መሣሪያውን ገዝተው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ታቅዶ 50 ግብር ከፋዮች የገዙ ሲሆን አፈጻጸሙም 36.49 በመቶ ዝቅተኛ ሆኖ ተገምግሟል።

“የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን በክልሉ የሚገኙ ግብር ከፋዮችን ኢ-ታክስ ለማስጀመር በተያዘው ዕቅድ መሰረት የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ (E-Payment) በቴሌ ብር ክፍያቸውን መፈፀም እንዲችሉ በ59 ታክስ ማዕከላት በማስጀመር 20 ሺህ የሚጠጉ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በቴሌ ብር እንዲከፍሉ በማድረግ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ግብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡

“ዲጂታል መታወቂያ አፈፃፀምን በተመለከተ፥ አጠቃላይ እስከአሁን ለ51 ሺህ 081 ታክስ ከፋዮች ከዲጂታል መታወቂያ ቁጥር ጋር በማቀናጀት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር መስጠት ተችሏል። የተጣጣመ የታክስ አስተዳደር ማስፈንን በሚመለከት፥ በበጀት ዓመቱ እንደ ተቋም በሕግ ማዕቀፍ መሻሻል ተጨማሪ ገቢ ለክልሉ ለማስገኘት እና ፍትሃዊ የገቢ አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ ግብ ተቀምጦ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

“በመሆኑም በሩብ ዓመቱ 5 የታክስ ህግ ማዕቀፍ ለማሻሻልና ወቅታዊ ለማድረግ፣ 2 የተቋሙ የሰው ሀይል አስተዳደር መመሪያዎች በድምሩ 7 ለማሻሻል ታቅዶ 1 የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ እና 1 የገቢ ግብር አዋጅ ተዘጋጅቶ በማኔጅመንት ግብዓት ተሰጥቶበት ለክልል ምክር ቤት አቅርቦ ለማፀደቅ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

“የታክስ እና አገልግሎት ቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥራዎችን በተመለከተ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፥ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከየአስተዳደር እርከኑ በኦዲት ግኝት ከቀረቡ 20 ቅሬታዎች ውስጥ ለ9 ግብር ከፋዮች ምላሽ ተሰጥቷል። አፈጻጸሙም 45 በመቶ ሲሆን፤ ከቀረቡ 103 የመደበኛ ግብር አወሳሰን ቅሬታዎች ለ103 ግብር ከፋዮች አቤቱታ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው በመደረጉ መቶ በመቶ ማከናወን ተችሏል፡፡

“በተመሳሳይ ሁኔታ ከቀረቡ 15 የአገልግሎት ቅሬታዎች ውስጥ ለ15 ግብር ከፋዮች አቤቱታ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው በማድረግ ሙሉ በሙሉ ማሳካት ተችሏል። በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ከቀረቡ 138 የታክስና የአገልግሎት ቅሬታዎች ውስጥ ለ127 ግብር ከፋዮች አቤቱታ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው በማድረግ አፈጻጸሙ 92 በመቶ ሆኗል፡፡ አስራ አንዱ በኦዲት ግኝት የቀረቡና በሂደት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የሩብ ዓመቱ የአፈፃፀም ሪፖርት ያሳያል፡፡”

የህግ ተገዢነት አመራር ልህቀትና የግብር ከፋዮች አጠቃላይ ታሪክ ከማደራጀት ጋር በተያያዘ፤ በሥጋት ደረጃ መተንተን እና በከፍተኛ ሥጋት የወደቁ ግብር ከፋዮችን ለኦዲት የማስተላለፍ ሥራዎችን በተመለከተ፥ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሁሉም መምሪያዎች 938 የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች አጠቃላይ ታሪክ በደረጃና በንግድ ዘርፍ ለማደራጀት ታቅዷል ሲሉ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሰረት የ1 ሺህ 227 ግብር ከፋዮች መረጃ የማደራጀት ሥራ መስራት የተቻለ ሲሆን አፈጻጸሙም 131.81 በመቶ ነው፡፡ ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ 19.63 በመቶ ነው፡፡ የሩብ ዓመት አፈፃፀሙ እንደሚያሳየው፦ የአፈጻጸሙ ዝርዝር በመዋቅር ደረጃ ሲታይ ከየም እና ከሦስቱ ልዩ ወረዳዎች ውጪ ሁሉም መዋቅሮች በዕቅድ መሠረትና ከዕቅድ በላይ ማሳካት ችለዋል ሲሉ ማብራሪያቸውን አጠቃልለዋል፡፡