የዘንድሮው የአለም አቀፍ የህጻናት ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳውላ ከተማ በድምቀት ተከበረ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 02/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “የህፃናት ጥበቃና የመጫወት መብት ለሁሉም ህፃናት!” በሚል መሪ ቃል የዘንድሮው የአለም አቀፍ የህጻናት ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳውላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በአለም ዓቀፍ ደረጃ ለ36ኛ በሀገራችን ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ በዓሉ ሲከበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ካሴች ኤሊያስ በህፃናት ሁለንተናዊ እድገት ላይ መስራት የሀገሪቱን ተስፋ ለማፅናት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
የህፃናትን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ ለሀገር መሰረት የሆነ ትውልድ መገንባት ይገባል ብለዋል።
ለህፃናት ምቹ የሆነች ሀገርን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ለዛሬዎቹ ህፃናት በምናደርገው እንክብካቤ ይወሰናል ያሉት ኃላፊዋ፤ በዚህ ረገድ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም ገልፀዋል።
የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ጎበዜ ማደቦ፤ ሁሉም አካላት ለህፃናት ሁሉ አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም መብትና ደህንነት መጠበቅ በተቀናጀ መልኩ እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤሊያስ፤ አለም አቀፍ የህጻናት ቀን ስናከብር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለማስቆም ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት ይገባዋል ብለዋል።
የሳውላ ከተማ ከንቲባ ንጉሴ መኮንን (ዶ/ር)፤ የህጻናት መጫወቻ ስፍራ ለማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የክልሉ ህጻናት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ህጻን አዶናይ አማኑኤል፤ እኛ ህጻናት ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም የመዝናኛ ስፍራ ከተመቻቸ የተሻለ ዜጋ በመሆን የነገይቱን ኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ መረከብ እንችላለን ብላለች።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ ህጻናትና ትምህርት ቤቶች የምስክር ወረቀት፣ መዳሊያ፣ ዋንጫና የገንዘብ ሽልማት በዕለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል።
በመርሃ ግብሩ ህጻናት ላይ ጥቃት ከደረሰ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ነጻ የስልክ መስመር ይፋ እንደሚደረግና የህጻናት መጫወቻ ቦታ ርክብክብ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ በበጀት ዓመቱ ከአራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ
ከተማ አስተዳደሩ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የማምረቻ ሼድ ርክክብ አደረገ
በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እስከአሁን ባለው ለማህበረሰብ አገልግሎቶች 2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ