የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ በበጀት ዓመቱ ከአራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝ ገለፀ
በዞኑ በማዕድን ዘርፍ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም መምሪያው አስታውቋል።
የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚነወር ሃያቱ፤ መምሪያው በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ይህንን ገቢ ለማሳካት በተለይም በማዕድን ዘርፍ ከአሸዋ፣ ጥቁር ድንጋይ፣ ነጭ ድንጋይ፣ ጠጠር እና ከሌሎችም ማዕድኖች በበጀት ዓመቱ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የክረምት ወራትን ሳይጨምር ከ15 ሚሊዮን ብር ባላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል አቶ ሚነወር።
የዞኑን የገቢ አቅም ለማሻሻል ከማዕድንና ከቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው፤ በዞኑ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመካለከል ከዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ እና ፀጥታ መምሪያዎች ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ መሆኑን አቶ ሚነዋር አብራርተዋል።
በዞኑ እንደ ግራናይትና ፊልድ ኢስፓር የተሰኙ ሁለት ማዕድናት የተገኙና ጥናት እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ ህብረተሰቡን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል አቶ ሚነዋር።
አያይዘውም የማዕድን ዘርፉ ለዞኑ ኢኮኖሚያዊ ማደግ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራ የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀው በዘርፋ የሚጠበቀው ገቢ እንዳልተሰበሰበና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥትቶ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
የጉራጌ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው፤ ጉራጌ ዞን የበርካታ የግንባታ ማዕድናት ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በዞኑ ስምንት በአነሰተኛ ደረጃ ባለሀብት እና 243 በባህላዊ መንገድ በማህበር ተደራጅተው ማዕድን የማምረት ተግባር ላይ ተሰማርተው እሰሩ ሲሆን በዚህም ለ20 ሺህ ሰዎች የስራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
ዘንድሮ ሁለት ሺህ ስራ አጥ ወጣቶችን ለመደራጀት ታቅዶ በእስካሁኑ ሂደት ለ640 ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን የገለፁት የመምሪያው ኃላፊ፤ በዘርፉ የመንግስት ገቢ በተገቢው እንዲሰበሰብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።
እንደ ሃላፊው ገለፃ፤ ማዕድናት የሚመሰረትባቸው አካባቢዎች መልሶ በማልማት ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ በስነ ህይወታዊና በስነ አካላዊ ስራዎች አግሮ ኢኮሎጂውን መሠረት ያደረገ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።
አቶ አየለ አያይዘውም በዞኑ በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው እስከ 6 ወር ድረስ በአካባቢው ምንም ዓይነት ተግባር የማያከናውኑት ቦታው ተወስዶ በህግ አግባብ ለሌላ ባለሃብት እንደሚተላለፍ ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ገቢዎች መመሪያ የደንበኞች አገልግሎት፣ የታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ሷሊህ ጀማል፤ በዞኑ ለግንባታና ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚውሉ በርካታ የማዕድን አይነቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ በዘርፉ በሚገኘው ምርት ላይ የህብረተሰቡንና አምራቾችን ጫና በማይፈጥር መልኩ ታክስ እየተሰበሰበ እንደሆነ ገልፀዋል።
መምሪያው በማዕድን ዘርፍ በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መልኩ ተደራጅተው የሚሰሩ አምራቾች ለመንግሥት የሚገባውን ገቢ በወቅቱ እንዲከፍሉ የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የዘንድሮው የአለም አቀፍ የህጻናት ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳውላ ከተማ በድምቀት ተከበረ
ከተማ አስተዳደሩ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የማምረቻ ሼድ ርክክብ አደረገ
በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እስከአሁን ባለው ለማህበረሰብ አገልግሎቶች 2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ