በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እስከአሁን ባለው ለማህበረሰብ አገልግሎቶች 2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ

በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እስከአሁን ባለው ለማህበረሰብ አገልግሎቶች 2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ

የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ልማት ማህበሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሌብ ካንሳ ተናግረዋል።

በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሁሉ ዓቀፍ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ከማሳደግ አኳያ ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን የአካባቢው ማህበረሰብ ተናግረዋል።

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ‎ከመንግሥት ጎን በመሆን የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አንዳንድ የደምባ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች አድንቀዋል።

‎ከነዋሪዎች መካከል የኡባ ጵዝጎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማርቆስ ሸላ እንደተናገሩት፤ ልማት ማህበሩ መንግስትን በመደገፍ በሁሉም ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሰራ መቆየቱን አንስተው በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ የተፈጠረውን ስብራት ለመጠገን የቁሳቁስ ድጋፍን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ ያለ ትልቅ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

‎ከጫና ገርፋ ቀበሌ አቶ ሙኦ ሙንታ እና ከቦርዳ ቀበሌ አቶ ዮሴፍ መኮንን እንደገለፁት፤ ልማት ማህበሩ በወረዳው የሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን አንስተው ከእነዚህም በሁለቱ ማዕከላት የተከፈተው መድሀኒት ቤት የጤና አገልግሎቱን ከማሻሻል ረገድ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

‎መድኃኒት ቤቶች በመከፈታቸው መደሰታቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ መድሀኒት ቤቶቹ ከመድሀኒት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙ ችግሮችን እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።

‎በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ዘርፈ ብዙ ፀጋዎችን በመጠቀም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንደሚገባው ነዋሪዎቹ አስገንዝበዋል።

‎በጎፋ ልማት ማህበር የደምባ ጎፋ ወረዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሌብ ካንሳ በበኩላቸው፤ ልማት ማህበሩ በበጎ አድራጎት በርካታ የትኩረት መስኮች መኖራቸውን ጠቅሰው በትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ሴቶችና ህጻናት ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት በመስራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝና የህዝቡም ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

‎ተቋሙ አጭር ዕድሜ ያለው ቢሆንም በአሁን ቆይታው ከ2 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሚሆን ወጪ በማውጣት ትኩረት አድርገው ከሚሰሩባቸው ዘርፎች በዋናነት በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ካሌብ ገልፀዋል።

‎ማህበሩ በየአመቱ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን ከመደገፍ በዘለለ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ግብአት በሟሟላት ሰፊ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አቶ ካሌብ አስረድተዋል።

‎ለቀጣይ ልማት ማህበሩ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን የገለፁት አቶ ካሌብ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአባላት ብዛትና የልማት ማህበሩን የውስጥ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ድጋፌ ድክሬ – ከሳውላ ጣቢያችን