በክልሉ ባለፉት 5 ወራት ከ133 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ
ቢሮው በክልሉ ያሉ ዕድሎችና ፀጋዎችን በመጠቀም የኢንተርፕራይዝ ዘርፍን ውጤታማ በማድረግ የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ማገዝ እንዳለበትም ጥሪ አቅርቧል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ስራ አጥ ዜጎችን በከተማ፣ በገጠርና በአምራች ዘርፎች በማደራጀት የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
ቢሮው ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራን ውጤታማ ለማድረግ ከበጀት ዓመቱ መነሻ ጀምሮ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ልየታ በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱንና በዚህም በተከናወኑ ግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ነው የገለፁት።
በበጀት ዓመቱ ለ400 ሺህ ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን የጠቀሱት አቶ ሙስጠፋ ይህንኑ ተከትሎም ባለፉት 5 ወራት በከተማ፣ በገጠርና በአምራች ዘርፎች ለ193 ሺህ 104 ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንና ከእነዚህም ዜጎች መካከል 133 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ነው ያስረዱት።
ለዕቅዱ ስኬታማነት በተደረገው ጥረት በተለይም በክልሉ በከተማና በገጠር ያሉ ፀጋዎችን እና ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም የተሰራው ስራ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ያሉት የቢሮ ኃላፊው አቶ ሙስጠፋ፤ በዘርፉ የተመዘገቡ ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።
በየደረጃው ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የክህሎት ስልጠናን ጨምሮ የገበያ፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የድጋፍና ክትትል ስራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ለአምራች ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት የቢሮ ኃላፊው፤ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በማስመልከት በወልቂጤ ከተማ በተዘጋጀው ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ ከ31 ሚሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።
ስራ አጥ ዜጎች ስራን ሳይንቁ በተለይም የአካባቢን ጸጋ በመጠቀም ጠንክረው ከሰሩ ሀብት በመፍጠር ለሌሎችም የሀብት ምንጭ መሆን እንደሚችሉ ገልፀዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በቅንጅት መሥራትን የሚጠይቅ ዘርፍ በመሆኑ በክልሉ ያሉ ዕድሎችና ፀጋዎችን በመጠቀም የኢንተርፕራይዝ ዘርፍን ውጤታማ በማድረግ የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ማገዝ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በተለያዩ የልማት መስኮች ሴቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ
“ከጂኦ ስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ቃል የካፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አመራር አባላት የስልጠና መድረክ ተጀመረ
የዘንድሮው የአለም አቀፍ የህጻናት ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳውላ ከተማ በድምቀት ተከበረ